ስንብት

26 March 2014
Source: Sodere.com

ስንብት

by Sirak Robele Gari

በሲራክ ሮበሌስንብት

የህሊናው ቁንጢጥ ከእሷ ከሚያገኘው ስጋዊ ደስታ ጋር ቢታገልም ሊያሸንፍ አልቻለም።ላለፉት ሁለት ወራት ሁሌም እሷን ካገኘ በኋላ ራሱን ቢጠላም፣የሚሰራው ሥራ ፍፁም ስህተት መሆኑን ቢገነዘብም እንደገና ደግሞ የወጣት ትኩስ ደሙ ለብ ብሎ አንገቷን ሲያቅፍ ያ ሁሉ ፀፀት፣ያ እንደመርፌ ጠቅ የሚያደርገው የህሊና ቁንጥጫ ይዶለዱማል።እሷ ከስሩ ሆና ረጃጅም ጣቶቿ ጀርባውን ሲዳስሱት፣አንገት ስሩን የሚያጥለቀልቀው ትኩስ ትንፋሿ ሲሞቀው፣ከስሜት አፋፍ ላይ የሚመጣው ቁርጥ ቁርጥ የሚለው ድምጿ በጆሮው ሲያንሾካሹክ የምን ፀፀት፣የምን ጭንቀት! ለሱ ልዩ አለም ነበር።

 

አስናቀ ንጋቱ አጠገቡ የተጋደመችውን አዜብ መንግስቱን ከአንገቱ ቀና አለና ተመለከታት።ግራ ክንዷን ደረቱ ላይ ጣል አድርጋዋለች። ጥቁር ጸጉሯ ከትራሱ ተርፎ ወደታች ተዘናፍሏል።ትላልቅ አይኖቿ በሸለብታ እንቅልፍ ተከድነው ወፈር ወፈር ያሉት ከንፈሮቿ ፈገግ ያሉ መስለዋል።ገፅታዋ የእርካታ ደስታ የተጎናጸፈ ነበር።አስናቀ ይህን አንዴ በጣም ወዶት የነበረውን አሁን ግን ንቀትና ፍቅር የተደበላለቀበት ስሜት የሚሰጠውን የሴት ፊት ለረጅም ጊዜ አተኩሮ ከአየ በኋላ እንደወትሮው በአንድ ጊዜ ንቀትም፣ፅያፌም፣ርህራሄም፣ፍቅርም ተሰማው።ቀስ ብሎ ግራ ክንዷን በቀኝ እጁ ያዘና ከደረቱ ላይ አወረደው።አዜብ አልነቃችም።ቀስ ብሎ ከአልጋው ወረደና የክፍሉን መስኮት ከፈተው።የሌሊቱ ቀዝቀዝ ያለ ነፋስ ራቁት ደረቱን ሲዳስሰው መንፈሱ በመጠኑ ተረጋጋ።ምናልባት ብርድ ይመታው እንደሆነ እንኳ አልታሰበውም።

 

አይኖቹን አፍጥጦ በተክለ-ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አደባባይ ዙሪያ እንደሌሊቱ የጠቋቆሩ ቡትቶዎች ለብሰው የተጋደሙትን በረንዳ አዳሪዎች ይመለከት ገባ።  ማን ያውቃል? በነዚያ እንደምድር አሸዋ በበዙ የተባይ ሰራዊት የታጠሩ፣እነዚያ ሰማያዊ-ጥቁር እድፋም ሸማዎች የተከናነቡት ድሃ ወጣቶች፣ከእኔ ዝቅ ያለ መካከለኛ ኑሮ ከምኖረው፣አዜብን የመሰለች ወጣት ካወጣሁት የአንደኛ አመት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የበለጠ ድሎት አላቸው ይሆናል።ከውጪ የደላው መስሎ ደህና እየበላና ደህና እየለበሰ ነገር ግን የጭንቅላቱን ውስጥ ጭንቀትና ፀፀት ከሚቦረቡረው ብላቴና ይልቅ መንፈሱን ምንም ይሉኝታና ጭንቀት ሳይደባብሰው አካሉን ተባይ የሚቦረቡረው ድሃ ሳይሻል ይቀራል?!  ይሁን እንጂ እነዚያ በረንዳ አዳሪዎች በአካልም በመንፈስም የተደቆሱ ይሁኑ አይሁኑ አስናቀ አላወቀም።

 

አዜብን የተዋወቀ ሰሞን ምንኛ ወዷት እንደነበር አስታወሰ።ይህ ፍቅሩ ሌሊት አላስተኛ ቀን አላስቀምጥ እያለ እንዴት አሰቃይቶት ነበር?አዜብ ሠራተኛ ነችና ቀን በቀን ባለመገናኘታቸው እንዴት በናፍቆት ይንገበገብ ነበር? ያ ማንበብ የሚወደው ወጣት ንባቡን እንኳ እርግፍ አድርጎ ትቶ ዘወትር የሚያስበው ስለውድ አዜብ አልነበረም?በየቀኑ እንዳይደውልላት የሱ ዘወትር ሃያ ሳንቲም ማውጣት አዳጋች በመሆኑ ብቻ ሳይሆን እሷንም ላለማስቸገር በማለት በሳምንት ሁለቴ ሊደውልላት እሷም በጓደኛው በዘውዱ በኩል ስልክ ልትደውልለት ተስማምተው ነበር።ታዲያ በነዚያ ቀናት ሁለት አስር ሳንቲሞችን ይዞ ስልክ ፍለጋ በየቡናቤቱ ይንከራተት አልነበረም?ደግሞስ ጓደኛው ዘውዱን ስንቴ ነበር   “ አዜብ ዛሬ ስልክ ደውላልኛለች? ” እያለ ከሰላምታ በፊት የጉጉት ጥያቄ ያቀረበለት?

 

አቤት! ያቺ የሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ምን ያህል የተቀደሰች ቀን ነበረች?!ምንም እንኳ አዜብ እሱ ገንዘብ እንዲያወጣ ባትፈልግም ወንድ ነውና እንዴት ሁሌ ሴት ታጋብዘኛለች በሚል የዋህ ስሜት ታጭቆ፤እንደ ደሞዝተኞች ሊያወጣ ባይችልም በዘውዱ እርዳታና እሱም ከየትም የሰባሰባትን ገንዘብ ይዞ ከአዜብ ጋር ያሳለፋቸው ቀናት ትዝታ ቀላል አይደለም።ሆቴል ገብተው ከበሉ ከጠጡ በኋላ ሂሳብ ለመክፈል ወደኪሱ እጁን ሰደድ ሲያደርግ አዜብ በማሾፍና በፍቅር ፈገግታ “ እረፍ!ጉረኛ!” እያለች ከቦርሳዋ ቀያይ ብሮች አውጥታ የከፈለችባቸው ቅዳሜዎች የተክለ-ሃይማኖትን አካባቢ ጨለማ እየሰነጣጠቁ ከትዝታ ጓዳው ብቅ አሉበት።አስናቀ በርህራሄ ፈገግ አለ።አዜብ እኮ ለሱ ምንጊዜም ክፉ አይደለችም።

 

ከውስጡ ጋር የሚያደርገውን ሙግት ገፋበት።ዛሬ የግንኙነታቸውን አቅጣጫ ለመወሰን ነበር የቀጠራት።ይሁን እንጂ ገና ሲያያት ሳቂታ ገፅታዋ ትጥቁን አስፈታው።ለሳምንታት ያህል ሲጨነቅበት፣ሲያወጣ ሲያወርድ ቆይቶ ሐሙስ ዕለት ማታ ይህንኑ እያሰላሰለ ከሰፈሩ ተነስቶ በዋቢሸበሌ ሆቴል አድርጎ፣ሰንጋተራን አቋርጦ፣ኢትዮጵያ ሆቴልን አልፎ በአብዮት አደባባይ ዞሮ ወደ ቤቱ በመመለስ ላይ ሳለ ነበር ውሳኔውን ያጸደቀው።ጊዜ አላጠፋም።በማግስቱ ወደ አዜብ ቢሮ ስልክ ለመደወል የመጀመሪያው ሰው እሱ ሆነ።ለቅዳሜ ማታ ተቃጠሩ።ስልክ መነጋገሪያውን ሲያስቀምጥ ትልቅ እፎይታ ተሰማው።በወሰደው ቆራጥ እርምጃም  እንደመኩራራት ሳይለው አልቀረም።ግን…ግን…አዜብ ከተቀጠረችበት ሰዓት ሁለት ደቂቃ ሳታሳልፍ ከታክሲ ዱብ ስትል ያ ሁሉ ወኔው ዝናብ እንደመታው ለም አፈር  እየተሸረሸረ…እየተሸረሸረ…ሲሄድ ተሰማው።

 

ለተከራየው ክፍል አስቀድሞ እሱ ከፍሏል።ለእራታቸው አዜብ ከፈለችና ወደ መኝታ ክፍል ሲገቡ አስናቀ እንደከበሮ የሚደልቅ ልቡን ድምጽ ለማፈን ይመስል በቀኝ እጁ ልቡን ሸፍኖ ውሳኔውን ሊነግራት አቆብቁቦ ነበር።ለዛ ያለው ጣፋጭ ጨዋታዋ ግን ሊያንቀሳቅሰው አልቻለም።ከጥቂት ሰዓቶች በፊት ቁርጡን ለመንገር ምላ ተገዝታ የነበረችው ምላሱ ሀሳቧን ለውጣ የምታወራው የተለመደውን ጨዋታ ብቻ ሆነ።ልፊያ ተጀመረ።ከዚያ ሙቀት።በኋላም…

 

ከአንድ መንፈቅ በላይ በፍቅር አሳልፈዋል።በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ ተዋውለዋል።አዜብ እንደምትወደው ያውቃል።እሱም ቢሆን የዛሬውን አያድርገውና በንጹህ ፍቅር ወዷት ነበር።እና ሲተዋት በፀብ ሳይሆን በመግባባት እንዲሆን ይፈልጋል።ፍቅሩ የዛሬው አይነት ሳይሆን የመንድምና የእህት ፍቅር መሆን አለበት።ሸጋ ፀባይ አላት። ሸጋ ፀባይ ያላትን ልጅ እህት ማድረግ ደግሞ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም።አስናቀ ጥቅሙን የተመለከተው በገንዘብ አኳያ አይደለም፤በሰው ልጆች ግንኙነት አንጻር እንጂ!ስለዚህ ከአዜብ ጋር ተወያይቶ የፍቅራቸውን ምዕራፍ ለመዝጋትና አዲስ የልውጥ ፍቅርና ወዳጅነት ምዕራፍ ለመክፈት ነበር-ውሳኔው።

 

ዛሬ የመጨረሻ በሆነው ቀን የመጀመሪያውን አስታወሰ።ፀሀያማ የመጋቢት ቀን ነበር።አዲስ አበባ በወርቃዊ የፀሀይ ብርሃን ተጥለቅልቃለች።አልፎ አልፎ ነጫጭ ጉሞችን ያንጠለጠለው ሰማያዊ ሰማይ ከወትሮው የራቀ መስሏል።የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተዳርሷል።አስናቀ ከጧት ጀምሮ እስከምሳ ሰዓት ድረስ ያለማቋረጥ አጠናና ከምሳ በኋላ ረፍት አስፈለገው።ቤት መዋል አላሰኘውም።ሲኒማ እንዳይገባ ገንዘብ አይበቃውም።ያለ አላማ በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ ሲንቀዋለል እግሩ ለገሀር አደረሰው።የቁጥር 27 አውቶብስን በር አንቀው የተሰለፉትን ሰዎች ተመለከተ።ግማሹ ይጋፋል፤ይጓሸማል፤ገሚሱ ኪሱን አንቆ ይዞ ይራገማል።ሌላው ይስቃል።አስናቀ አብሮ ሳቀ።አብሮ እንደሳቀ ሁሉ አብሮ ለመጋፋት ከተሳፋሪዎቹ ጋር ተቀላቀለ።ያለችውን አንዲት ብር አውጥቶ ቲኬት ቆረጠ።ሰማንያ አምስት ሳንቲም ተመለሰለት።ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ብሄረ-ፅጌ መናፈሻ ውስጥ ራሱን አገኘ።አንድ ስሙኒና አንድ አስር ሳንቲም ተረፉት።

 

አንዴ እየተቀመጠ፣አንዴ እየተዘዋወረ በነፋስ የሚጋሽቡትን ዕፅዋት፣አበባ ለመቅሰም የሚራወጡትን ነፍሳት ከሸመደደው ባዮሎጂ ጋር ለማጣጣም እየሞከረ ሲመለከለት ቆየና ድንጋይ አግዳሚ ላይ አረፍ አለ።ወዲያው አንዲት ቀጠን ያለች ቀይዳማ ወጣት አጠገቡ ተቀመጠች።ዞር ብሎ እንደዋዛ ተመለከታት።በትላልቅ አይኖቿ ታስተውለው ነበር ።አፈር ብሎ ፊቱን መለስ አደረገ።ያደረገችውን ነጭ ጫማ፣ዳለቻ ቀሚስና ቆዳ ኮት የጎሪጥ ከመመልከት ግን አልቦዘነም።ለረጅም ጊዜ በፀጥታ ተቀመጡ።

 

“ የዚህን አበባ ስም ታውቀዋለህ? ” ትህትናን በተላበሰ አፋራም ብጤ ድምፅ ፀጥታውን የገሰሰችው እሷ ነበረች።

ደንገጥ ብሎ ዞር አለ።በሌባ ጣቷ ወደ አበባው እያመለለከተች፣ፊቷ ወዛ ብሎ ፈገግ ብላለች።አበባው ወይነ-ጠጅ ነው።አጫጭሮቹ አጥሮች ላይ ተንጠልጥሏል።ሐረግ መሆኑ ቢገባውም ስሙን አያውቀውም።

“ እኔ እንጃ…አላውቀውም…”  ድንግርግር እያለው መለሰ።

“ ደስ ሲል! ” አለች ልጅቷ።

 

በአዎንታ ራሱን ነቀነቀ እንጂ ከሌሎቹ አበቦች የበለጠ ደስ ይላል ብሎ አላሰበም።ይህ ነበር በእሱና በአዜብ መካከል የተደረገው የመጀመሪያ የቃላት ልውውጥ።እና አስናቀ ወይነ-ጠጅ አበባ ሲያይ ትዝ የምትለው አዜብ ናት።ቀይ ዳማ መልኳ፣ቀጠን ያለ በመሆኑ መካከለኛ የሚያስመስላት አጠር ያለ ቁመቷ፣ሳቂታ እና አንዳንዴም ቁምነገራም የሚሆኑ  አይኖቿ ትዝ ይሉታል።ወይነ-ጠጅ አበባና አዜብ ለምን ጊዜውም በአስናቀ አይነ-ህሊና ውስጥ ተነጣጥለው የማይታዩ ውሁድ ሆነው ቀርተዋል።

 

ከዚያ በኋላ የት እንደምትሰራ፣ዛሬ የውይይት ክበብ ፕሮግራም ቢሆንም የውይይት ክበቡን ሊቀ መንበር አስፈቅዳ ወደዚህ መምጣቷን ነገረችው።ዛሬ ስራ ስለበዛ ራሷ በጣም መታመሙን፣የአበቦች ሽታና የዕፅዋት ዕይታ ሊያድናት የሚችል መሆኑን በመተማመን ወዲህ መምጣቷን አጫወተችው።አሁን ተቀራርበዋል።አስናቀ የነበረው ስሜት በምንም ያልተበረዘ ነበር።የሷን ስሜት አላጤነውም።

“ ሰፈርህ እዚሁ ቅርብ ነው እንዴ? ”

“ አይ አይደለም።ወደ ከፍተኛ 4 አካባቢ ነው። ”

“ የት እንደሆነ እንጃ እንጂ አንድ የሆነ ቦታ ያየሁህ ይመስለኛል። ”

“የት ሊሆን ይችላል? ምናልባት መንገድ ላይ አይተሽኝ ይሆናል።የመስሪያ ቤትሽ ቅርንጫፍ የት ነው? ”

ቦታውን ነገረችው።

 

“ ወደዚያ እንኳን አላዘወትርም…” ብሎ ገና ሳይጨርስ “ ብቻ የሆነ ቦታ አይቼሃለሁ።” አለች ፈገግ ብላ።በዚያ ፈገግታ ውስጥ የተደበቀ ነገር አስናቀ አልተመለከተም።በእድሜ እንደምትበልጠው ገምቷል።እሱ ገና የሃያ አመት ጎረምሳ ነው።እሷ አንድ ሃያ ስድስት አታጣም።ጨዋታዋ እንዲሁ ጨዋታ ብቻ ነው ብሎ አሰበ።ግራ የተጋባው በደራ ጨዋታቸው መሃል “ አድራሻዬን ልስጥህና ደውልልኝ፤ያንተንም ስጠኝ! ” ባለችው ጊዜ ነበር።

 

መደናገሩን ሳያስነቃ ስሟንና አድራሻዋን ማስታወሻው ላይ መዘገበ።ማስታወሻዋ ላይ መዘገበች።

 

አንድ የሌሊት ሠራተኞችን የያዘ ሰርቪስ መኪና እያጓራ ሲያልፍ አስናቀ ከቁም ህልሙ ብንን አለ።ምናልባት አዜብም ነቅታ እንደሆነ በማለት ወዳልጋው ተጠጋ።አልነቃችም።የመኪናው ድምፅ በእንቅልፍ ልቧ አስናቀ ተኝቶበት ወደነበረው   የአልጋ ጫፍ ይበልጥ እንድትጠጋ ነበር ያደረጋት።ቀኝ ክንዷ የአልጋውን ጫፍ አጥብቆ ይዟል።የታጠፈው ጉልበቷ ጫፍ ከአንሶላው ስር ብቅ ብሏል።ያልሟሸሹት ወጣት ጡቶቿ አንሶላው ስር አፍጥጠዋል።ገፅታዋ እንደቅድሙ ፍፁም ሰላማዊ አልነበረም። በትንሹ ሸብሸብ ብሏል።አጠገቧ የሚታቀፍ ገላ በመጥፋቱ ይሆን? ብሎ አሰበና በቀስታ መስኮቱን ዘግቶ እንዳይቀሰቅሳት በዝግታ አንሶላው ስር ገባ።ጧት…ጧት…ሲነጋ ያደርሰኛል፤ያኔ ሁሉን ነገር እነግራት ይሆናል ብሎ አስናቀ ምናልባትም ለሀምሳኛ ጊዜ አሰበ።ወጣት ሰውነቱ  ግን ይህን መሳይ ሙቅ ገላ መተው ሞኝነት አይሆን ይሆን? አለው።በፀጥታ ለረጅም ጊዜ ተጋደመ።የአዜብ ትኩስ ሰውነት ቀስ በቀስ ቀጭን በራድ ሰውነቱን ሲለኩሰው ተሰማው።ራሱን ማታለሉ ይሆን? ‘ በቃ ለመጨረሻ ጊዜ!’ አለና ጥብቅ አድርጎ አቀፋት…

 

– 2 –

 

ያለወትሮው ዝናቡ ችክ ብሎ ይዞታል።ሰማዩ ላይ ነጭ ጉም ከዳር ዳር  ተጋግሮበት ሰማያዊ መልኩ ለአመል ያህል አይታይም።ከዝናቡ ጋር ተደምሮ የሚነፍሰው ቀዝቃዛ አየር ከሰውነት በታች እስከጅማት ድረስ ይሰማል።አስናቀ አንድ አልበረደውም።ትኩስ ትንፋሹን ቡልቅ እያደረገ ደጋግሞ ሰዓት ይጠይቃል።የቆመበት ግሮስሪ ባለቤት እንደመሰልቸት ሳይለው አልቀረም።ለስምንት ሃያ አምስት ጉዳይ…ሩብ ጉዳይ…ስምንት ሰዓት ከአምስት…በመጨረሻ ባለሱቁ ፊቱን በመሰልቸት ቅጭም አድርጎ  “ ስምንት ሰዓት ተኩል!” ሲለው ነበር አስናቀ ሰዓት ሲጠይቅ አራተኛ ወይም አምስተኛው መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነዘበው።አፈር አለ።

 

ጧቱን በካፊያ ጀምሮ ጎርፉን ካወረደው በኋላ የሚሰረስር ብርድ ይዞ የመጣው ዝናብ አሁንም አላባራም።ብን ብን እያለ ይወርዳል።እንዲሁ ለክፋት ሲል ብቻ በሚያዝያ ዘንቦ እንዳትመጣ አሰናክሏት ይሆን? ብሎ አሰበ።ወይም ረስታው ይሆናል።አለበለዚያም እሺ ያለችኝ እንዲያው ከማስቀይመው ብላ ነው።አልመጣችም።ማታለሏ ይሆን?

 

የስልክ ንግግራቸውን አስታወሰ።አንድ ሁለት ሳምንታት አለፉና በሰጠችው አድራሻ መሰረት ደወለላት።ስልኩ የተይዟል ምልክት አሰማው።ጥቂት ቆይቶ እንደገና ደወለ።ልቡ ምቱን ጨመረ።ተይዟል።በብስጭት መነጋገሪያውን ሰቀለ።እዚህ መገተር አልፈለገም።ሌላ ቀይ ስልክ ባሻገር ካለው ቡናቤት ሲያይ ወደዚያ አመራ።በመሃሉ የአዜብ ስልክ ይለቀቃል ብሎ አስልቶ ነበር።ደወለ፤መስመሩ ተይዟል።ጣጣ እኮ ነው! አስናቀ ብስጭትጭት አለ።ጥቂት ቆይቶ እንደገና ደወለ።ይጠራል።እፎይታ…ልብ መሰቀል..ፍርሃት…

“ ሃሎ!”

“ ሃሎ! እባክዎትን አዜብን ነበር…”

“ አንዴ ይጠብቁ!”

ጥቂት ዝምታ፤በልብ መሰቀል የተዋጠ ፀጥታ።ክብደቱን ከቀኝ ወደ ግራ ከግራ ወደቀኝ እግሩ እየቀያየረ ጠበቀ።

“ ሄሎ? ”

“ሃሎ..አዜብ?…አስናቀ ነኝ…”

ከማይታየው ቴሌፎን የመጣለት ደስታ የተቀላቀለበት መልስ አስደሰተው።ፍርሃቱ ሁሉ እንደጢስ በነነ።

“ እንደምንድነሽ? ” አስናቀ ፈገገ።

በአጭሩ ከሰላምታና ከጥቂት ትርኪምርኪ የቃላት ልውውጥ በኋላ “ መቼ ይመችሻል?” ሲል ጠየቀ።

የመጣለት መልስ ፈጣንና አጭር ነበር።ልቡ በደስታ ሲመላ ተሰማው። “ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ? እሺ…እ…ልክ በስምንት ሰዓት። ጥሩ…እሺ ሱቁ ጋር እጠብቅሻለሁ።የቀጠሮ ማክበር ጉዳይ ግን…” ፈገግ አለ።

“ ኦኬ ቻዎ..” ስልኩን ሲዘጋ ከደስታው ጋር የተደበለች ትንሽ ትርጉሟ የማይገባ ፍርሃትስ ነበረችበት?

 

ሰዓት እንደገና መጠየቅ አሳፈረው።በልቡ ግን ለዘጠኝ ሩብ ጉዳይ ይሆናል ሲል ገመተ።ቀስ በቀስ ሳይታወቀው ሆዱ ንዴትና ቅያሜ ማርገዝ ጀመረ።በዝናቡ መሃል ፍትልክ እያሉ የሚያልፉትን ታከሲዎች ጥርሱን እያፋጨ ይቆጥር ገባ።ከአሁን ጀምሮ ስድስት ታከሲዎችን እቆጥራለሁ፤ከዚያ በቃ! የራሷ ጉዳይ! ብሎ ወሰነ።አንድ…ሁለት…ሶስት…አራት…አምስት…ከአሁን ወዲያ የሚመጡትን ታከሲዎች እንዳላየ ሆኖ ለማሳለፍ ፈለገ።ጭንቅላቱ ግን ልቡን ታዘበው።እና ስድስት…ስድስተኛዋ ታክሲ ቆመች።የሱም ልብ እንደመቆም…አንዲት ቀጠን ያለች ወጣት ብቅ አለች።ያስናቀ አይን ደግሞ ፍጥጥ…እሷን ተከትለው አንድ ረጅም ሽማግሌ አብረው ወጡና ወደ መንደሩ ውስጥ ገቡ።አስናቀ በቅያሜ ፊቱን አኮማተረ።የተረገመ ዝናብ! እሱ ነው ያሰናከላት!

 

ብዙ ጊዜ አላለፈም፤ሰባተኛዋ ታከሲ ፍትልክ ብላ ካለፈች በኋላ አስናቀ ልሂድ ልቆይ እያለ በሚያመነታበት ወቅት ስምንተኛዋ ታክሲ ቆመች።ከፊት በር አንድ ወጣት ብቅ አለ።ከኋላ ደግሞ አንዲት አሮጊት ወጡ።ክፍት አለው።ራሷ ላይ ቀይ ላሰቲክ አጥልቃ ከቆዳ ኮቷ ስር ረዘም ያለ ቀሚስ የለበሰች ቀጭን ወጣት ብቅ አለች።በመከፋት ተመልታ የነበረችው የአስናቀ ልብ በደስታ ተመላች።አይኖቿ የሚቃዡትን ወጣት በዝምታ ሊያያት አልደፈረም።ቀልጠፍ ብሎ ተጠጋት።በፈገግታ ተቀበለችው።ኪሱን ደባበሰ።የዘውዱ ቤት ቁልፍ በተቀመጠችበት ቦታ አለች።ጣጣ አላበዛም።

 

“ ወደቤት እንሂድ!” አላት በጥቂቱ እንደማፈር እያለ፤ ከሰላምታ በኋላ።

 

አልመለሰችለትም፤እጇን ክንዱ ውስጥ ሸጎጥ አደረገችና መስማማቷን በዝምታ ገለፀች እንጂ።በዝናቡ መሐል ቁልቁል መንገድ ጀመሩ።ስለምን እንዳወሩ አስናቀ የሚያስታውሰው ነገር የለም። ለምን እንዳረፈደች ብቻ የሆነ ነገር ብላዋለች፤የጎረቤት ለቅሶ ወይም ድንገተኛ እንግዳ።ስለዝናቡ እንዳላወራች ግን እርግጠኛ ነበር።ብን ብን ብሎ እየወረደ ጎፈሬ ፀጉሩን እንዳራሰውም  አልተሰማው። ከአምስት ደቂቃ በኋላ ቤት ደረሱ።

 

“ ይኸውልሽ የውሸት ቤት!” አለ በፈገግታ “ የዱርዬ ቤት! ” በሩን ከከፈተ በኋላ በግማሹ ቀድሞ ገባና ወገቧን ደገፍ አድርጎ አስገባት።

“ ኧረ! ይሄ ተገኘቶ ነው?! ” መለሰች እሷም በፈገግታ።

 

አሮጌ አግዳሚ ላይ ተቀመጠች።ጊዜ ሳያባክን አስናቀ የጋዙን ምድጃ ለኩሶ ሻይ ጀበና ጣደ።ቴፕ ሪኮርደሩ ተበላሽቶ ነበርና ሙዚቃ አልጋበዛትም።አዜብ የጎሪጥ ሳይሆን በግልጽ ጠባቧን ቤት ዙሪያዋን ቃኘቻት።ግርግዳው በዶንያ ተለብዷል።ከእንግሊዝኛ መጽሄት ላይ በልዩ ልዩ ቅርጽ የተቆራረጡ ስእሎች አልፎ አልፎ በሰያፉ ተለጣጥፈዋል።የፊት መስታወቱ አጠገብ በልብ ምስል የተቀረጸ እንጨት አይ ላቭ ዩ የሚል ተለጥፎበት በክር ተንጠልጥሏል።አዜብ ፈገግ አለች።ኮርኒሱ የዶንያ ሆኖ በሚገባ ካለመወጠሩም በላይ ማታ ማታ ብቅ የሚሉት አይጦች የበለጠ አርግበውታል።ሳጠራው ወለል ላይ አንድ ትልቅ ሳጥን፣አንድ የሸንበቆ ጠረጴዛና ቁምሳጥን ከአንድ አግዳሚና ከሁለት ወንበሮች ጋር ይታያሉ።አልጋው አጠገብ የዘውዱን ፎቶ ከበው በዛ ያሉ ጉርድ ፎቶግራፎች በመስታወት ሆነው ኮሞው ላይ ተደርድረዋል።አንድ ክራርና አንድ አኮርዲዮን ከኮሞው በላይ ግርግዳው ላይ ተሰቅለው ዘውዱ ሙዚቃ ወዳድ መሆኑን ይመሰክራሉ።አዜብ ይህን ሁሉ በአጭር ቅፅበት አዳርሳ ፊቷን መለስ ስታደርግና አስናቀ ዳማ መጫወቻውን ይዞ ሲጠጋ አንድ ሆነ።

“ ለመሆኑ ዳማ ጎበዝ ነሽ? ”

“ ምንም አልል፤ እስቲ ሞክረኝ! ” ፈገግ አለች።

 

ተጫወቱ።አንዴ አሸነፋት።ሁለቴ አሸነፈችው።ሁለቱም ከተመሰጡበት ጨዋታ የተላቀቁት ሻዩ ሲገነፍል ነበር።አስናቀ ብድግ ብሎ ጀበናውን አነሳ።ከዚያ ብርጭቆዎቹን ሲያቀራርብ እሷ ራሷ ሻዩን በሁለት ብርጭቆዎች ቀዳች።አስናቀን ደስ አለችው።ግልፅነቷንና ከኩራት ፍፁም ነጻ የሆነ ፀባይዋን ወደደው።ኬክ ከነካርቶኑ አመጣና ቅርጫቱ ጠረጴዛ ላይ አስቀመጠ።

“ ጓደኛህ ብቻውን ነው የሚኖረው? ” ብላ ጠየቀችው።

“ አዎን! ” አለና ሳይታወቀው ወደ ዘውዱ ፎቶ አየት አደረገ።

“ ባሪያ ጓደኛ ነው ያለህ። ” በፈገግታ።

“ ጓደኛዬን ባትሰድቢብኝ ግን ደስ ይለኛል።” በቀልድ።

 

ሻዩን ግማሽ አላደረሱትም።ሁለቱም እንደመግነጢስ ተቃራኒ ጫፎች ሲሳሳቡ ተሰማቸው።በሚያወሩበት ወቅት እሱ አሷን አሷ እሱን ሲያዩ አይኖቻቸው ሟሙተው ወደ አንድ ጥንድነት  የሚቀየሩ መሰሉ።ልቦቻቸው በጣም ይመቱ፣ደማቸው በፍጥነት ይፈስ ጀመር።የጾታ እጢዎቻቸው ተግባራቸውን በአንክሮ ማከናወኑን ተያያዙት።

 

አዜብ ከአሁን አሁን ጠየቀኝ በማለት ልቧ ተንጠለጠለ።የሴትነትን ግንብ አጥር ንዳ ለማለፍ አልቻለችም እንጂ የመጀመሪያዋ ጠያቂ እሷ በሆነች ነበር።ግንብ የማያፈርስ አቅሟን አወቀችና አስናቀ ይህን ለዘመናት የቆየ ግንብ ንዶ ከሷ እንዲቀላቀል በጉጉት ጠበቀችው።ውስጧ እየጮኸ በዝምታ አለያም በአይኖቿ ተማጸነችው።በጨዋታዋ ገፋፋችው።በቃ! ከዚህ በላይ አስናቀ ሊታገስ አልቻለም።ይሉኝታ ከዚህች ውብ ልጅ ይበልጣል እንዴ? ፍርሃትስ? ፍርሃቱን ደግሞ የአዜብ ጋባዥ አይኖች፣ለስላሳ ድምጽና ለዛ-ሙሉ ጨዋታ አሸነፈው።

 

እጇን ይዞ ወደ አልጋው መራትና ጫፉ ላይ ተቀመጡ።የወጣት ሰውነቷ ሙቀት ከሩቁ ይጋረፋል።አንዴ አየት አደረገችውና አንገቷን ደፋች።ጨዋታዋ እዚህ ላይ አከተመ።ዝምታ ብቻ! ሴት እኮ በዝምታም ትጋብዛለች!ቀኝ ክንዱን ትከሻዋ ላይ ጣል ከማድረጉ የአዜብ ቀጭን ገላ ደረቱ ላይ መጥቶ ዘፍ አለ።ከንፈሮቻቸው ወዲያው ተገናኙ።እየተንገበገቡ የሚጎርሱትን የአዜብን ከንፈሮች መልሶ እየጎረሰ በአንድ አስረኛ አእምሮው አዜብ እንዴት ነው የምትጣፍጠው? የሚል ሀሳብ ሽው አለበት።ወዲያው መተኛት አልፈለገችም፤ትንሽ ልፊያ አስፈለጋት!የሁለቱም ሙቀት ከገደቡ ሊያልፍ ጥቂት ሲቀረው፣ ሁለቱም የየራሳቸው ጌቶች መሆን ሲያቅታቸው፣የልፊያውን ስልት ቀየሩ።በጠባቧ ክፍል ውስጥ ፍጡርም ያለ አልመሰለ።ፍፁም ጸጥታ፤ጣፋጭ ደስታ!

 

ከደቂቆች በኋላ ጸጥታው በአዜብ የእርካታና የመደሰት ሳቅ ተናጋ።የሷን ቃጭል ድምጽ ተከትሎ የአስናቀ ጎርናና ድምፅ ተሰማ።እንደበፊቱ አልጋው ጫፍ ተቀመጡ።እሷ ቀና  ብላ እሱ ቁልቁል ይተያያሉ።አሁን በአይኖቻቸው ውስጥ የቅድሙ ተኩሳታዊ እሳት አይታይም።በእርካታ አይነ-ርግብ ለጊዜው ተሸፍኗል።አሁን በዚያ ትኩሳት ፈንታ ቀዝቃዛ ነገር ግን ጥልቅ ደስታ ተተክቷል።አይኖቻቸው ፍቅርን ያንጸባርቃሉ።

 

በጨዋታቸው መሐል “ ኡ ብሄረ ጽጌ! ብሄረ ጽጌ አገናኘን ! ” አለችና አዜብ በግንባሯ ጭኑ ላይ ተደፋች።

ፀጉሯን በጣቶቹ እያበጠረ “ አዎን አዎን ስለዚህ ባለውለታዬ ነው! ” አለ አስናቀ አፋራም ፈገግታ እያሳየ።ደግነቱ አዜብ አላየችውም።በግንባሯ ጭኑ ላይ እየተሻሸች “ ለኔም! ለኔም!” አለች እንጂ።

“ አስናቅዬ ገና እንዳየሁህ እኮ ነው የወደድኩህ ! ” እየፈገገች ቀና ብላ ጎላ ጎላ ባሉት አይኖቿ እየተመለከተችው ነበር አዜብ ይህን የተናገረችው።የአስናቀ ጠቆር ያለ ፊት በእፍረት መውዛቱን አላጤነችም፤ በቤቱ ውስጥ የሰፈነው ጠይም ጨለማ ሸፍኖታል።

“ እኔ ግን…እውነቱን ለመናገር… ” አለ አስናቀ እያመነታ “ እንዲህ አይነት ጓደኝነት እንጀምራለን ብዬ አላሰብኩም ነበር..አሁን ግን እኔም እወድሻለሁ። ”

‘እወድሻለሁ’ የሚለውን ቃል መናገሩ ከበደው፤ ድንገት ነበር ያመለጠው።መውደድ ቢጀምረውም ምን ያህል እውነት እንደሆነ አልገባውም።እና በራሱ ቅር ተሰኘ።በጠይሙ ጨለማ ውስጥ በደስታ ቦግ ቦግ  ያሉትን የአዜብን አይኖች ሲያይ ነበር ቅሬታው የተጋመሰለት።እሷን ይህን ያህል ካስደሰተ የኔ መሳሳት ምንም አይደል ሲል ተጽናና።

 

አዜብ የበለጠ ፈካች፤ይበልጥ ጣፈጠች።ቀልድና ድሪያዋ ሁሉ ከበፊቱ በአጠፌታ ጨመረ።አስናቀ ያወቃት ለጥቂት ሳምንታት፣አብሯት ሲጫወት ደግሞ ይሄ ገና ሁለተኛው መሆኑን ረስቶ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ የሚያውቃት፣ሃሳቡንና ስሜቱን ለረጅም ጊዜ ያካፈላት የልብ ጓደኛው መሰለችው።ማን ያውቃል! እስከዛሬ ካገኘኋቸው ጥቂት ትናንሽ ልጃገረዶች ይበልጥ የበሰለች፣ሃሳቤን የምትደግፍ፣የምትነቅፍና የምታርም ወጣት ማግኘቴ ይሆናል ብሎ አሰበ።ልቡ በደስታ ሲመታ ተሰማው።ከደስታ ስሜቱ ጋር ደሙ ሞቅ አለ።ከጥቂት ደቂቆች በፊት ያጣጣመው የአዜብ ጣፋጭነት ታሰበው።እንደገና አቅፋው ጣዕሟን እንድትሰጠው፣እንደገና አቅፏት ጣዕሟን እንዲቀበል ተመኘ።እና ቀጫጭን ጠንካራ ክንዶቹ በትከሻዋ ዙሪያ ተጠመጠሙ።

 

– 3 –

 

የመጣችው ወንድሞቿን ሸውዳ መሆኑን ነገረችው።ሁለት ታናናሽ ወንወድሞች እንዳሏት ከዚህ በፊት አጫውታው ነበር።ባለዘለበት ቡናማ ቦርሳዋን ወንበሩ ላይ አስቀምጣዋለች።መነጽሯን አውልቃ በእጇ ይዛዋለች።ከላይ ደረብ አድርጋ የነበረውን ሹራብ ወንበሩ መደገፊያ ላይ ሰቅላዋለች።ትናንሽ እግሮቿ ከጥቁር ታኮ ጫማዎቿ ተለይተው አልጋው ላይ ይታያሉ።አስናቀ በጀርባው ተንጋሎ አቀብ የአዜብን ጨዋታ ይኮመኩማል።

“ … ሙት እውነቴን ነው።እኔ እንደሴቶች የምጠላው የለኝም።ወንዶችን ሽርኬ ማድረግ እችላለሁ።ሴቶችን ግን…”

“ እንዲያው አንድም የሴት ጓደኛ የለሽም? ”

“ የውሸት ጓደኞች ናቸዋ ! ”

“ መቼም አንድ የሴት ጓደኛ ያስፈልግሻል።ለወንድ ልታጫውቺ የማትችይው ብዙ ነገር እኮ አለ።”

“ እሱስ ነው…” አለችና አዜብ “ አይ! አይ! ብቻ እኔ ሴቶችን አልወድም፤እናቴን ጭምር!” በማለት ራሷን ተቃረነች።

 

በጎኑ ገልበጥ ብሎ መነጽሯን ሲቀበላት የሴት ጥላቻሽን ሳይኮሎጂሰቶች ትርጉም ይስጡት እያለ ነበር በልቡ።ካነበባቸው አንድ ሁለት የሳይኮሎጂ መጽሀፍት ያገኘውን ቁምነገር እዚህ ሊጠበብበት አልፈለገም።ፈገግ አለችና መነጽሯን ስትሰጠው ኮሜዲኖው ላይ አስቀመጠው።በቀኝ እጇ ፊቱን መታ ስታደርገው ሳብ አድርጎ ሳማት።መለሰችለት።

 

“ ከኔ ጀምሮ ሴቶች ጥሩ አይመስሉኝም ! ” አስናቀ ቢተው አዜብ ርዕሷን አልተወችም።

“ ግን ለምንድነው ሴቶችን የጠላሽው? ”

“ እኔ እንጃ! የሚጀምረው ለእናቴ ካለኝ ግዴለሽነት ይመስለኛል።ስለሷ ወደፊት እነግርህ ይሆናል።በርግጠኝነት ግን ለጥላቻዬ መነሾው ምን እንደሆነ ለመናገር አልችልም።ጨዋታቸው እንኳ ይቀፈኛል።ሁሌ የሚያወሩት ስላወጧቸው ወንዶች፣ስለ ልብስና ስለጫማዎቻቸው፣ስለሚቀቧቸው ቅባቶች ብቻ ነው።እኔ ስለማልቀላቀላቸው ‘አንቺ እልም ያልሽ ኋላ ቀር ነሽ-አሮጊት!’ ይሉኛል።እኔና አንተ ስንተዋወቅ አንድ አራት ወር አልፎናል፤እስቲ አንድ የሴት ጓደኛ አስተዋውቄህ አውቃለሁ?…ለኔ ግጥሜ ወንድ ነው!”

 

“  እሱማ የወንድ ጓደኛም አስተዋውቀሽኝ አታውቂም እኮ! ” አላት እንደቀልድ።

 

በሳቅ አሳለፈችው።አዜብ ስለሴት ጥላቻዋ ስትነግረው ይህ የጀመሪያዋ አልነበረም።የአዜብ ፊት ለአስናቀ ውድ ቢሆንም ጥርጣሬ ገባው።በግል የሚያውቃቸው ጥቂት ሴቶች የራሳቸውን ጾታ በጣም ይጠላሉ።እና ፀባያቸው ልቅ ነው።አስናቀ ሳይፈልግ በአዜብ ገጽታ ላይ ዝሙተኛ የሴት ምስል ይከሰትበት መሰለው።ንጽህት አዜብን ሲፈልግ ሌላዋ አዜብ ብቅ ትልበት ጀመር።በቁጣ ይህን ምስል አሽቀንጥሮ ለመጣል ሲታገል “ ሴቶች የሚያወሩት ስላወጧቸው ወንዶች፣ስለሚቀቧቸው ቅባቶች…” የሚለው አነጋገሯ ረዳውና በዘማዊቷ አዜብ ምትክ ጨዋና ታማኟ አዜብ ስትተካበት ተመለከተ።ወይስኤሌክትራ ኮምፕሌክስ ይኖርባት ይሆን? አስናቀ ይህን ሁሉ ያሰበው በአጭር ቅጽበት ነበር።

 

“ ለመሆኑ አዜብ ባል ብታገቢ ምን ያህል ታማኝ ትሆኝለታለሽ? ” ብሎ ጠየቃት በፈገግታ።

 

ፊቷ ተለዋወጠ።እስካሁን ድረስ ቁልቁል ይመለከቱት የነበሩት አይኖቿ ስጋት ተነበበባቸው።ደረቱን ይደባብሱት የነበሩት እጆቿ ባሉበት ቆሙ።ይህ የስሜት መለዋወጥ ትርጉሙ አልገባውም።ለአጭር ቅጽበት በዝምታ ተዋጠች።

 

“ ምነው ምን ነካሽ? ” አስናቀ በግማሽ መደንገጥ በግማሽ መገረም ጠየቀ።

“ አ-አይ ምንም! ” አለችና ለአጭር አፍታ ዝም! ከዚያ “ ስለትዳር ሲነሳ ሁሌ እንዲህ ያደርገኛል።የትዳር ዋዛ አለመሆን እየታሰበኝ ይሆናል።” ብላ ተነፈሰች “ ብዙም ባይሆኑ ጥቂት ወንዶች እናግባሽ እያሉ መጥተውልኝ ነበር።ግን እኔ የምፈልገውን አይነት ሆነው አልተገኙልኝም።አንዱ ቤትና መኪና ኖሮት ፀባይ ይጎድለዋል።አንዱ ደግሞ ፀባዩ ጥሩ ይሆንና ጠጪና አጫሽ ሆኖ ይገኛል።ባይገርምህ አላገባህም ካልኳቸው ወንዶች መሐል አንዱ ዛሬ ኮሚሽነር ሆኗል።እኔ ባክህ ባል ሳላገባ የምኖር አይነት ሴት ሳልሆን አልቀርም።”

“ መቼም በሁሉ የተሟላ ሰው አይገኝም።ስለዚህ ከጉዳቱ ጥቅሙ፣ከመጥፎነቱ ጥሩነቱ፣ከጉድለቱ ሙሉነቱ የሚያመዝነውን ይዘሽ መቀመጥ ያንቺ ፈንታ ነው።” እንደሶስተኛ ሰው ቀርቦ እሱ የወደዳትን ሴት ለሌላ አሳልፎ መስጠቱ መሆኑ ለጊዜው አልታሰበውም።“ ለብቻ መኖር ጥሩ አይደለም! ”

“ አይ አስናቅ ወንዶች ትታመናላችሁ? ”

“ በጅምላ የሚሆን ነገር የለም አዜብ።ለሁሉም ነገር ልዩ አለው።ወንዶች በሙሉ ታማኞች አይደሉም ማለት ያዳግታል።ሴቶችም በሙሉ ቀጣፊዎች ናቸው ማለት አይቻልም።”አለ አስናቀ እጇን በፍቅር እየደባበሰ።

“ ይሁን እስቲ! ” በረጅሙ ተነፈሰች።

“ ግን እኮ የጠየቅኩሽን አልመለሽልኝም! ”

“እሱን በኋላ! እሱን በኋላ! ” አለችና አዜብ እላዩ ላይ ወደቀች።ወዲያው አንሶላው ውስጥ ገቡ።ከፀጉሩ ጀምሮ መላ ሰውነቱን እየደባበሰች ስታጫውተው እንደፍቅረኛ ለስላሳ እንደ እህት ሩህሩህ ነበረች።

“ ባለ ባችለሯን አወጣህ ማለት ነው? ” አለች እየሳቀች ከፍቅር ድሪያ በኋላ በጀርባዋ ተንጋላ ደረቱን በአይበሉባዋ እየደባበሰች “ አሁን  ሰዎች ሲያዩ እኮ ይሄ ልጅ በየት በየት ተሰባብሮ አገኛት በማለት ይገረማሉ።”

“ ወረቀትሽን እኮ ግንባርሽ ላይ ለጥፈሽ አትዞሪም! ” አላት። በልቡ ‘አንቺ እንጂ እኔ አላገኘሁሽም እኮ!’ እያለ።ሳቀች።

 

ምናልባት ይቺ ልጅ የወደደችኝ ትኩስነቴ አጓጉቷት ይሆን?ከሌሎች ሰዎች ጋር ብዙ ተዳርታ ሰልችቷት ይሆን ከኔ ጋር የተወዳጀችው?የሚል ሀሳብ ወደጥርጣሬ የአእምሮ ኪሱ ጥልቅ አለበት።

“ እስካሁን ስንት ወንዶች ታውቂያለሽ? ”

“ ለምን ጠየቅከኝ? ” አለችው በእንግሊዝኛ።

“ለመጠየቅ ስል! ” በእንግሊዝኛ መለሰላት።

“ ሶስት።”

“ብቻ? ”

“ ምነው? አነሰ? ለኔ ግን ብዙ ነው።አንዱና የመጀመሪያው ያው የነገርኩህ ልጅ ነው-እንትኔን ያስረከብኩት።” ፈገግ አለች “ ሁለተኛውን ተወው..እንዲያው ዝም ብሎ ነው።ሶስተኛውን ያገኘሁት ከአራት ወር በፊት እዚያው ብሄረ ጽጌ ነው። ጣፋጭ፣ሚጢጢ ባሪያ ነው።”

በፈገግታ ጡቶቿን ጭምቅ እሽት አደረገ።እውነቷን መሆኑን ተጠራጥሯል፤ሌላ ጥያቄ ግን ማቅረብ አልፈለገም።

“ አቤት አንተ ልጅ! ” አለች ፀጉር ማብቀል የጀመረ ደረቱን እያሻሸች “ ደረትህ እንደብረት አንሺ ሰፊ ነው።እኔ እንዲህ አልጠበቅኩህም ነበር።ጠቅላላ ስራህ ደግሞ እንደልጅ ሳይሆን እንደበሳል ሰው ነው።”

ግልፅነቷ አስደነቀው።ምንም አልተናገረም።ለአጭር ቅጽበት ፀጥታ ሆነ።

“ ምናባክ ይዘጋሃል? ተጫወት እንጂ! ” አለች በጭኗና በክንዷ ገፋ እያደረገችው “ አሁንስ ወንድሞቼ የሚሉኝን አስታወስከኝ።”

“ ምን ይሉሻል? ”

“ አንቺ እንደሆንሽ ሰው ስትመራርጪ እስከመቼም አታገቢ።ቢያጋጥምሽም አንቺ ስትለፈልፊ ዝም የሚል አይነት ዝጋታም ደባሪ ነው።”

“ ልክ እንደኔ? ”

አዜብ ለመልሱ ፈጣን ነበረች። “ አንተ እንኳን አታበዛውም እንጂ ትጫወታለህ።ትቀልዳለህ።እነሱ የሚሉት እኮ  ጨርሶ ዝጋታሙን አይነት እና ይህ ሳያንሰው ደግሞ ሰካራምና አጫሹን ነው።” ጭኗን ጭኖቹ ላይ ክንዷን ደረቱ ላይ አድርጋ ጥብቅ አደረገችውና “ አስናቅዬ አንተ እኮ አታጨስ፣አትጠጣ።በዚያ ላይ ደግሞ የማይሰለችህ እና እንደ ብረት ጥንክርክር ያልክ ነህ።” አለችው።

“ አዜብ የጊዜው ጊዜ አንቺ የምትፈልጊውን የሚያሟላ ባይሆንም ይበልጡኑ አንቺ የምትወጂውን የምታገኚበት ወንድ ማወቅሽ አይቀርም።” አላት ለሱ የቀረበውን ምስጋና ችላ ለማለት እየሞከረ፤እንደውነቱ ግን ምስጋናው እያስደሰተ አሳፍሮት ነበር።አዜብ በአስተያየቱ ትደሰት አትደሰት አልተገነዘበም።ንግግሩን ቀጠለ “ ምናልባት የምታገኚው ሰው የገንዘብ ድሃ ግን ልበ ትልቅ ይሆን ይሆናል።”

“ ከአንተ በላይ ልበ-ትልቅ ያለ ይመስልሃል? ” ትንፋሿ አንገት ስሩን ይሞቀዋል። “ አስናቅዬ አንተ እኮ ልበ-ኩሩ፣አይናፋርና በዚያው ጎን  ደግሞ በራስህ የምትተማመን ልጅ መሆንህ እንዴት እንደሚያስደስተኝ ታውቃለህ?ይኸውልህ እኔ የምፈልገው ገንዘብ አይደለም፤ እኔን የሚወድ፣ ከኔ ሌላ ሴት የማይፈልግ ወንድ ብቻ ነው።በወደድኩት ሰው እቀናለሁ።የሚያስቀናኝን ወንድ አልወድም።የማገባው ሰው እኔን ብቻ እንዲያይ፣ ከኔው ጋር ብቻ እንዲውል እፈልጋለሁ።”

“ መቼም ባለቤትሽ ያንቺ እስረኛ መሆን አይፈልግም።ዋናው በሁለታችሁ መሐል ያለው  ፍቅርና መተማመን እንጂ ያንቺ ዘበኝነት ነው እንዴ ባልሽን ከመወስለት የሚመልሰው? ”

“ በጣም ትክክል ነህ።እኔም ብሆን ከተቆጣጠሩኝ እልህ ውስጥ እገባለሁ።ሆኖም በባሌ ቀልድ የለም! እቀናለሁ። በዚያ ላይ ደግሞ ወንዶች አትታመኑም።”

 

ባለፉት ጥቂት ወራት የአስናቀ አይን ባጋጣሚ ወደሴቶች ሲወረወር በአዜብ ፊት ላይ ያስተዋለውን ቅያሜ አሁን  አስታወሰ። ከሷ ጋር ሲሆን መጠንቀቅ ነበረበት።

 

“ ባልሽም እኮ ነጻነትን ይፈልጋል።ምናልባት የማትታመኚው አንቺ ራስሽ ስለማትታመኚ ይሆናላ! ” አስናቀ ይህን የተናገረው እንደዋዛ፣ቀልድ አክሎበት ቢሆንም ምን ያህል የስሜት መጎዳት አዜብ ላይ እንዳስከተለ አልተመለከተም።

 

“ እ-ሱ ሳይሆን…” አለችና ለረጅም ጊዜ ዝም አለች።ክፍሏ መጨላለም ጀምራለች።ሰዓቱ እየገሰገሰ ሄዶ ጨለማ ጥቁር ገጹን አስቀድሞ ገና መድረሱ ነበር።እስከምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ውጪ አምሽተው ወደ ሆቴላቸው ለመመለስ ቅድም ተስማምተዋል።ሰዓቷን ተመለከተች።

 

“ ሰዓት ደርሷል እንውጣ አስናቅዬ! ” ከንፈሩን በረጅሙ ሳመችው።

***

ወደውጪ ሲወጡ ቀዝቀዝ ያለው የምሽት ነፋስ ፊታቸውን ገረፋቸው። እጇን ክንዱ ውስጥ አስገባችና በጣም ተጠጋችው።አፍቃሪ እጇ ክንዱን ሲደባብሰው ደስታ ሰጠው።መኪኖች ይራወጣሉ።ገና በጊዜ የሰከሩ መንገደኞች ይወለጋገዳሉ። በሳምንቱ መጨረሻ ለመደሰት ቋምጠው የነበሩ ፍቅረኞች ተያይዘው አለም ዘጠኝ ይላሉ።እነ አስናቀ ግን የሰሙትና ያዩት አልነበረም።የሚያዩት፣የሚሰሙት የእርስበርሳቸውን ተወዳጅ መልኮችና ድምፅ ነበር-ሌላ ምንም!

 

አዜብ ፊቷን ሸፈን ያደረገችበትን ያንገት ልብስ አስተካከለች።በልደታ አድርገው፣ሜከሲኮ አደባባይን ዞረው ሰንጋ ተራ ሲደርሱ ታክሲ አስቁመው ገቡ።ከጥቂት ደቂቆች በኋላ ሲኒማ ኢትዮጵያ አዳራሽ ውስጥ ነበሩ።ፊልሙ ገና መጀመሩ ነበር።የቆየ ፊልም ነው።ቀጭን ረጅም ልጃገረድ ከረጅም ለግላጋ ወጣት ጋር በፈረስ ትጋልባለች።ከኋላ አምስት ፈረሰኞች ይከተሏቸዋል።ጠላቶቻቸው መሆናቸው ነው።ፍቅረኞቹ ለረጅም ጊዜ ከጋለቡ በኋላ ለሁለት የተቀመጡበት ፈረስ ይደክምና ጠላቶቻቸው ደርሰው ይይዟቸዋል።ከመሀላቸው አንድ ጠብደል ሰው ይወጣና ወጣቱን ካልገደልኩ  ብሎ ይጋበዛል።ይገላግሉትና እስረኞቹን ይዘው ወደሰፈር ይመለሳሉ።ታሪኩ ገባቸው።ወጣቱ ልጅቱን ከማትወደው ባሏ አስኮብልሎ መጥፋቱ ነበር።አስናቀ በልጅቷ ስራ እንደመብሸቅ አለ።አዜብ ለልጅቷ አዘነችላት።

 

ፊልሙ እንዳለቀ አዜብና አስናቀ እጅ ለጅ ተያይዘው ወጡ።ታክሲ አልነበረም።ነፋሻማውን አየር እየተቀበሉ ቁልቁል መውረድ ነበረባቸው።ተደሰቱ እንጂ አልተከፉም።አስናቀ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ከአዜብ ጋር ፊልም ያየባቸውና በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ አብረው የተንሸራሸሩባቸው ቀናት እጅግ ውስን ናቸውና ብርቆቹ ነበሩ።አዜብ አብዛኛውን ጊዜ እሱና እሷ ብቻ፣ከሰው ተለይተው ያላቸውን ጊዜ በፍቅር ማሳለፍ ነበር የምትመርጠው። ‘አንተን ከሌሎች ጋር መጋራት አልፈልግም!’ ነበር የሁልጊዜ ቀልድ-አዘል ምክንያቷ።ስለተመለከቱት ፊልም አንዳንድ ሀሳብ መሰንዘር ጀመረ።አዜብ ደስ ያላት አትመስልም።እሷ መጫወት የፈለገችው ሌላ ሌላ ነበር፤ስለከተማዋ ውበት፣በዚህ ከዋክብት በተፈነጣጠቁበት ጨረቃማ ሰማይ ስር አስናቀን በአይናቸው የሚጋሯት እንስታት በሌሉበት ማታ ከሱ ጋር ተቃቅፋ መሄዷ ምን ያህል ያስደሰታት ስለመሆኑ።

 

በርግጥም ምሽቱ ዕፁብ ድንቅ ነበር።ከዋክብት በህዋው ላይ ተዘርተው ወለል ላይ የተበተነን የማሽላ ቆሎ ያስታውሳሉ።የስድስት ሰዓትን ፀሃይ የምታስንቅ ባትሆንም የምታስታውሰው ጨረቃ ብርሃኗን በምልዓት ሰጥታ የጎዳናውን መብራቶች ተስተካክላለች።በአዲስ አበባ ላይ የወረደውን ጥቁር-ሰማያዊ ጨለማ አግልላ የራሷ ግዛት በማድረግ በሰፊው ይዛዋለች።የምሽቱ ፊልም አዜብ ልብ ውስጥ የነዛውን ጨፍጋጋ ስሜት ሳይቀር ጠልቃ ገብታ ለመበታተን  ሃይል አግኝታ ነበር።

 

ዕፁብ ድንቅ ምሽት!ጣፋጭ ፍቅር!

 

 

 

–   4 –

 

ከቀን ወደቀን ፍቅር እየሞቀ ቢሄድም አስናቀ አንድ ስሙን የማያውቀው ድብቅ ስሜት ይጎረብጠዋል።ይህ ስሜት የተወለደው ከሚያደርጓቸው ተራ ጨዋታዎች ነበር።ሁሌ ለሚጠይቃቸው ጠለቅ ያሉ ጥያቄዎች የሚያገኘው መልስ ቀልድና ድንጋጤ መሰል ነገር ያዘለ ቸልታ ነበር።አዜብ በቀጠሮ የምትቀረው አልፎ አልፎ ቢሆንም ለዚያ ምክንያት በማቅረቧ ተከራክሯት አያውቅም።ምክንያቷ ባያሳምነውም እንኳ ክርክር አስፈላጊ መስሎ አልታየውም።

 

አንድ ቀን ስልክ ደወለላትና ሊያገኛት እንደሚፈልግ ነገራት።መቼ መምጣት እንደምትችል ደውላ እንደምትነግረው ገለጸችለት።ነገር ግን ሳምንቱን ሙሉ አልደወለችም።አሁንም የደወለው እሱ ነበር።ሳትደውል የቀረችው ስራ በጣም ስለበዛባት መሆኑን በመግለጽ ይቅርታ ጠየቀችው።ተቀበላት።ሳይገናኙ አስራ አምስት ቀናት አለፉና አስናቀ ልቡ አልችልልህ ቢለው ደወለላት።ደውላ እንደምትቀጥረው ብትነግረውም አላደረገችውም።አንድ ሌላ ሳምንት አለፈ።

 

አሁን የአዜብ ወረት እዚህ ላይ እንዳበቃ ወሰነ።አንድ ቀን አግኝቷት በሰፊው ከተወያዩ በኋላ ሊተዋት አሰበና ፍላጎት የሌለውን ሰው መጎትጎት አስቀያሚነቱን ተረድቶ ሃሳቡን ለወጠ።እናም የእሱና የእሷ ፍቅር በመደምደሙ ወስኖ የልቡን ቁስል እያስታመመ በጸጥታ ለመቀመጥ ቆረጠ።

 

ይሁን እንጂ ቁስሉን ማስታመም እንዲህ ቀላል አልሆነለትም።ያስባታል፣ያስታውሳታል፣እንዲያውም አንዳንዴ ስልክ ለመደወል አለያም ቢሮዋ ድረስ ለመሄድ ይቃጣዋል።ይሁን እንጂ ስለክብር ያለው ስሜት አሸንፎ  ከአዜብ ጋር በቀጭኑ ሽቦ ሳይገናኙ ሌሎች ሁለት እንደክፉ ቀን የረዛዘሙ ሳምንታት አለፉ።

 

ቀኑ መሽቶ በነጋ ቁጥር ስለ አዜብ ያለው አመለካከት በንዴትና በጥላቻ እየተሞላ ይሄድ ነበር።አዜብ ወሲብ የሚያጓጓት ወረተኛ ሴት መሰለችው።ደማም ተወዳጅ መልኳ የወረትን ገጽታ ሆነ የሚያሳየው።ከመቼው ሞቃ ከመቼው መብረዷ ፍቅሩን በጥላቻ እየበረዘው በሄደ ቁጥር አዜብ አንዴ ወዷት የነበረች ሴት ሳትሆን ከአላፊ አግዳሚው ጋር ስትዳራ በሩቁ የተመለከታት ዘማዊት መስላ ታየችው።እሱም ከእሷ ከተዳሩት ብዙ ወንዶች መካከል አንዱ መሆኑ ስለተሰማው በሞኝነቱ ሳቀ።ለስላሳ ጸባይዋ ታሰበው።ይህ ጸባይ ግን አብራቸው ልትጋደም ያሰበቻቸውን ወንዶች የምታጠምድበት ጠንካራ ወጥመድ ሆኖ ታየው።ፈገግታዋ ሲከሰት ብቅ የሚሉት ጥርሶቿ እንደሌሊት ጨረቃ ደምቀው ታዩት።ነገር ግን እንደበፊቱ ደስታና ፍቅርን አልመገቡትም፤በምትኩ ንዴትን እና ጽያፌን አዘነቡለት እንጂ።

 

ቀኑ መሽቶ በነጋ ቁጥር የአዜብ ስልክ መደወል አለመደወል ስሜት ሊሰጠው እንደማይችል አሰበ።እናም ዘውዱን መልእክት እንዳለው በመጠየቅ ማስቸገሩን አቆመ።በሴቶች ተፈጥሮ ግን መደነቁን አልተወም።አንዳንዴ ሃቀኝነቱ ያናድደዋል፤ያበሽቀዋል።እንደዘመኑ ወጣቶች ቀጣፊ ለመሆን ይከጅላል።እሱም ሴቶችን ለማታለል ያስብና ወዲያው ግን ይህ የመጨረሻ ደካማነት መሆኑ ትውስ ይለዋል።ፍቅር ጣፋጭ ነው ብለው ወደ አለም መድረክ ብቅ የሚሉትን ንጽህት ልጃገረዶች ስሜት መራር ማድረግ ትልቅ ወንጀል መሆኑን ያምንና ይህን በማሰቡ  ራሱን ይታዘባል።እኔ ራሴ መንፈሴን ማጠንከርና እንደልጆቹ አመጣጥ መቀበል አለብኝ! ይላል።ይሁንና ፍቅርን ወደፈለገበት አቅጣጫ ለመምራትና ሽክሙን ለማቅለል ሃይል አያገኝም።

 

ሴቶች ጥላ ናቸው፤ሲከተሏቸው ይሸሻሉ፤ሲሸሿቸው ይከተላሉ፤ የሚለው አባባል ምን ያህል ትክክል እንደሆነ ባያውቅም አንዳንድ ጊዜ በእውነትም ጥላ ሆነው ያገኛቸዋል።የኮራባቸውን ወንድ ዓይናቸው ደም እስኪመስል  እያለቀሱ ሲለምኑት የሚለማመጣቸውን ወንድ ደግሞ እንደ ለማዳ ውሻ ሲያደርጉት በማየቱ አስናቀ ከልቡ ያዝናል።እና እሱ ከለማኙም ሆነ ካስለማኙ  ላለመመደብ ይጥራል።በሴት ልጅ ላይ ተንኮልና ግፍ ሊሰራ፣ጉራ ሊነዛ ከቶ አይከጅልም፤ሊለማመጥም አይፈልግም።እስከዛሬ በህይወቱ የገቡትን ጥቂት ላጃገረዶች እንዳመጣጣቸው ተቀብሎ እንደአካሄዳቸው ነበር የሸኛቸው።

 

አንድ አርብ ዕለት አስናቀ ከመኝታው ሳይነሳ አረፈደ።ቀኑ ጨፍጋጋ ነበረ።ሰማያዊውን ሰማይ እያጨፈገገ የሚተመው ጥቅል ጉም በመስኮት በኩል ይታየዋል።አጠገቡ ከነበረው ወንበር ላይ መጽሃፍ አንስቶ ማገላበጥ ጀመረ።ዘውዱ በር አንኳኩቶ ሲገባ አስናቀ ከሁለት ገጽ በላይ አላነበበም ነበር።አዜብ ስልክ ደውላ እንደነበር ነገረው።ስሜት የሚሰጠውም ያልመሰለው ነገር አሁን ልቡን ጠቅ ሲያደርገው ራሱን ታዘበ።የደስታ ስሜት አልነበረም።የንዴትም አልነበረም።እንዲያው ብቻ ትርጉም ያላገኘለት ስሜት ልቡን ቁንጥጥ አደረገው።

 

“ ምን አለች? ”

“ አይ ብዙ አላወራንም።ለብዙ ጊዜ አለመተያየታችሁን ብቻ ነው የነገረችኝ።ግን አነጋገሯ ቅዝቅዝ ያለ ነበር።”

 

ከአንድ ወር በላይ ከተለያዩ በኋላ እሱ እሷን ሊረሳ በሚውተረተርበት ወቅት የሷ አስታውሶ መደወል የመንፈስ ጸጥታውን ገሰሰው።ነይ ሲላት ሳትመጣ እሱ ዝም ሲላት ለምን ድምጿን አሰማች?የቀድሞውን ግንኙነት ፈልጋ?ወይስ አንዴ የተዛመደችው ልጅ በመሆኑ ጾታዊ ግንኙነት እንኳ ቢቀር ዝምድናው እንዲቀጥል ብላ? አላወቀም።ዘውዱ ከሄደ በኋላ መጽሀፉን ለማንበብ ሞከረ።ነገር ግን የአዜብ ምስል ፊደሎቹን ሸፈነበት።አብረው ያሳለፏቸው ወራት ትዝ አሉት።መጽሀፉን ወርውሮ ተነሳ።ልብሱን ለባበሰና ቁርሱንም ምሳውንም አንድ ላይ በልቶ ውልቅ አለ።

 

በቅርቡ ሊደውልላት አልፈለገም።የሷ ምስል ደግሞ መመላለሱን በማዘውተሩ ስለ አዜብ ማሰላሰሉን አላቆመም።እንዳይደውልላትም፣እሷንም እንዳያስብ የሚያረሳሳው ነገር ፈለገ።ሲኒማ ቤት ገባ።እዚያ በሲጋራ እሳት ተከቦ፣በሲጋራ ጪስ ታፍኖ፣ጨለማ ውስጥ ተቀምጦ ተንቀሳቃሽ ስዕል ሲመለከት ጭንቀቱ ክፍል ይልለታል።እና አንድ ሳምንት ሙሉ በእንዲህ አይነት አሳለፈ።አንድ ረቡዕ ወደ ሲኒማ ቤት ሲያመራ እግረ መንገዱን አንድ ሼል ውስጥ የህዝብ ቴሌፎን ተመለከተ። ኪሱን ሲደባብስ ሶስት አስር ሳንቲሞች አሉት።አንዱን መለሰና በሁለቱ ደወለ።

 

በቅሬታ ከተመላ ሰላምታ በኋላ፣ከወዴት ጠፋህ ወዴት ጠፋሽ? በስቲያ ለቅዳሜ ቀጠራት፤ የሚሰማውን ሁሉ ሊነግራት።ቅዳሜ በተለመደው አዝጋሚነቱ ቢደርስም አዜብን ሳይዝ ብቻውን ነበር የመጣው።ተበሳጨ ፤ ለአዜብ የነበረው የፍቅር ትርፍራፊ በቅዝቃዜ ሲርስ ተሰማው።

 

ስለእሷ ማሰቡ ቀስ በቀስ እየቀነሰ፣በፍቅር ተመልቶ የነበረው ወጣት ልቡ በዝግታ በምሬት እየተለወሰ ቢመጣም አንድ ሐሙስ ዕለት ስልክ ከመደወል አልገታውም። አዜብ ቢሮ እንዳልገባች ተነገረው።

 

ከአራት ቀናት  በኋላ ያው ዘውዱ መጣና አዜብ ታማ ሆስፒታል መግባቷን፣ባለፈው ጊዜ የቀረችውም በዚሁ ሳቢያ መሆኑን ደውላ እንደነገረችው አረዳውና አስደነገጠው።ለመጀመሪያ ጊዜ ሄዶ ሲጠይቃት ትንሽ ድካም ብጤ ተሰምቷት ነበር።ከተለመደው ሰላምታና እግዜር ይማርሽ በቀር ምንም አላላት፤ብዙም አልቆየ።በሁለተኛና በሶስተኛው ቀን ግን ተሽሏት ነበር።ትንሽ የሚያስቸግራት ጊዜ እየለየ የሚነሳባት ራስ ምታት ነበር።አስናቀ ተመላልሶ በጠየቃት አንድ ሳምንት ውስጥ እንደተገነዘበው በተለይ ከቀኑ ወደ አስር ሰዓት አካባቢ ተሸፋፍና መተኛትን ትመርጣለች። እሱም ተሰናብቷት ይወጣል።አስናቀ ወደጧት አካባቢ ከሄደ የአዜብ የድሮ ፈገግታዋና ተጫዋችነቷ እንደምንጭ ይቀዳል።ከቀኑ አስር ሰዓት አካባቢ ግንባሯ ተከስክሶ፤ፊቷ ጠቋቁሮ አይኖቿ ገርበብ ማለት ሲጀምሩ አስናቀ ምን ሊያደርግላት እንደምትፈልግ ይጠይቃታል።ምንም! የሚያስፈልጋት መተኛት ብቻ ነበር።አብሯት ሊቆይ ቢፈልግም እንዲሄድ አጥብቃ ትጠይቀዋለች።

 

ሊላት የሚፈልገው ብዙ ነገር በልቡ ቢኖርም በህመም ላይ ሆና ምንም ወቀሳ ሊጀምር አልደፈረም።ነገር ግን እሷ ራሷ ነገሩን አቀለለችለት።ሆስፒታል ከገባች አስር ቀናት አልፏት ነበር።ጧት ነው-ሶስት ሰዓት።

“ አኩርፈህ ነው አይደለ የዘጋኸኝ? ” ብላ ጠየቀች።

ለሰከንድ ሃይለኛ ንዴት ሰውነቱን አላበሰው።ማፌዟ ነው ወይስ?…ደጋግሞ የደወለው እሱ ደጋግማ የጠፋችው እሷ! “ መዝጋት ማለት እንዴት ነው? ” መልሶ ጠየቃት።

 

ለቅጽበት በዝምታ አይኖቹ ላይ አተኩራ ተጋደመች።ትላልቅ አይኖቿ እንደወትሮው ቆንጆና ጨዋዎች ናቸው። ያባብላሉ።ልብ ውስጥ የወዳጅነት ስሜት ይጭራሉ።አስናቀም ከዚህ ስሜት የሚያመልጥ ጠንካራ ልብ አልነበረውም።አዕምሮው ግን ጠንክሮ ለማሸነፍ እተፍጨረጨረ ነበር።

“ ምን መልስ አለሽ አዜብ? ” አላት


እኔ ስላንተ ሳላስብ ያደርኩበት ቀን አልነበረም። ”

“ ለዚህ ነበር ስቀጥርሽ የቀረሽው? ”

“ አስናቅ ያልተረዳኸው ነገር አለ!እንዴት አድርጌ ልንገርህ?!” ፊቷ ላይ ያየውን ጭንቀት ትርጉም ሊሰጠው አልቻለም። “ ምን መሰለህ አስናቅዬ? ” አለች  እንደገና  ትላልቅ ጎድጓዳ አይኖቿን አስናቀ ጠቆር ያለ ፊት ላይ ለአፍታ ብቻ አሳርፋ።ጠበቃት።ዝም አለች።ትላልቅ አይኖቿ እሱን አልፈው የወዲያኛውን ግርግዳ ያያሉ ወይም አያዩም፤ብቻ አርፈውበታል።

“ እ..ምን ማለት ፈለግሽ? ” አላት ቢቸግረው።

“ ተወው አስናቀ ብዙ ያልገባህ ነገር አለ! ”

“ ሊሆን ይችላል አዜብ!መጀመሪያ ሳገኝሽ የዋህ እና ግልፅ አድርጌ ነበር የገመትኩሽ።አሁን ግን ሁለተኛ ማሰብ እንዳለብኝ ነው የተረዳሁት።አይኖችሽ ሌቦች ናቸው። ” አለና ተነፈሰ።ይህን ሲናገር የሚመለከተው ግርግዳው ላይ የተተከሉትን የዋሃን አይኖች አልነበረም።የሚያየው በመንገድ ላይ ሲሄዱ ሸጋ ሸጋ ወንዶችን ተከትለው የሚቀላውጡትን ሌባ አይኖቿን ነበር።ያኔ እንደዚያ አላሰበም ነበር።አዜብ በተሰወረችበት ወቅት ግን ትርጉም እንደነበራቸው ወስኖ ቆይቷል።

“ ዓይኖችሽ ሌቦች ናቸው? ” ብላ አዜብ በተበደለ ሰው ድምጽ ጠየቀች። “ እንዴት እንዲህ ልትል ቻልክ? ”

“ አይኖችሽን ስላየኋቸው!”ሲል መለሰ በቀላሉ “ አይነ-ሌባ ብቻ አይደለሽም!ሸዋጅም ጭምር ሳትሆኚ አትቀሪም! ”   ግን ምን ሆንኩ ራሱን ጠየቀ።

 

ለስላሳ ብልቷ የተመታ ይመስል አዜብ ፊቷ ላይ ስቃይ ተነበበባት።ወዲያው ደግሞ ትላልቅ አይኖቿ በንዴት አበሩ።በቅጽበት ስቃይና ንዴቷን በሳቅ ልትሸፍን ብትሞክርም አልታዘዝ ያላት ከናፍሯ አሳጣት።

“ ምነው አንተ! አሁንስ አናደድከኝ! ለመሆኑ ምን ዋሽቼህ አውቃለሁ? ምን ብዬ አታልዬህ አውቃለሁ? ሰው ሁሉ የሚለኝ ‘አዜብ የዋህ እና ግልጽ ናት’  እንጂ  አታላይ መባልን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንተ ነው የሰማሁት። ”

“ አዜብ የዋህነትሽን እኔም እመሰክራለሁ!ግን የየዋህ ዋሾ ደግሞ አይጣል ነው!”

 

በጀርባዋ ተኛችና ኮርኒስ ኮርኒሱን ትክ ብላ ትመለከት ጀመር።በጥቁር ጸጉር በተከበበ ጭንቅላቷ ውስጥ ምን ይመላለስ እንደነበረ አስናቀ አላወቀም።እሱ የተገረመበት ነገር ግን ሸዋጅና ውሸታም የሚሉት ቃላት በአዜብ ላይ ያሳረፉት በትር ጥንካሬ ነበር።

 

“ አስናቀ ይበቃኛል!ይበቃኛል! ከዚህ በላይስ አልችልም!’ አለች በጀርባዋ እንደተንጋለለች።

ርህራሄ ተሰማው።በቁጣ አልነበረም የተናገረችው- ከባድ ሸክም ተሸክሞ ሌላ ሲጨመርበት እየተሰቃየ በሚለምን ሰው ዜማ እንጂ።ሌላ ሊጨምር አልፈለገም።ሊናገር ያሰበው ግን ብዙ ነበር።

 

“ አስናቀ ይበቃኛል…በርግጥ በአንዳንድ ነገር ጥፋተኛ ልሆን እችላለሁ!ግን…” በሃዘን ፊቷን ወደ ግርግዳው አዞረች።

 

በፀጥታ ተቀመጠ።

 

“ ራሴ ተነሳብኝ!” አለች በቀስታ።

 

መልዕክቱ ገባው።ሲሰናበታት  “ ደግሞ ነገ እንዳትቀር!…” አለችው።

 

አዜብ ለአስናቀ ምስጢር ሆነችበት። ምስጢር ያጓጓልና ምስጢሪቱን ሊፈታት ፈለገ።ሊፈታት የሚችለው ደግሞ ርቆ ሳይሆን ቀርቦ በመወያየት መሆኑን ተረዳ።ቀን በቀን ለመገናኘት ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ ስላልነበረ ከሆስፒታሉ ዘበኞች ጋር ተወዳጀና ሲነጋ ወደ አዜብ ጋር ሆነ ሩጫው።ክረምት ነውና ጥናት አላወከውም።

 

አንድ ቀን ሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ አትክልት ቦታው ላይ ተቀምጠው ብዙ ተጨዋወቱ።ክፉ በጎ ተነጋግረው ከተለያዩ በኋላ በተከተሉት ሁለት ቀናት አዜብ ላመል ያህል ቀዝቀዝ ብላ ነበር።ዛሬ ተፍለቅልቃለች።

 

“ እኔ ” አለች አዜብ ጋቢዋን ተከናንባ፣እግሮቿን አጣጥፋ፣ጉልበቶቿን በሁለት እጆቿ ጠፍራ ተቀምጣለች።አስናቀ በጎኑ ጋደም ብሎ፣ክንዱን ተመርኩዞ አቀብ ያያታል።

“ እኔ ከዚህ በፊትም ሳልነግርህ አልቀረሁም።ለገንዘብ ብዬ በፍጹም አላገባም።ልውደደው፣ጸባዩ ይስማማኝ እንጂ ለምን ሊስተሮ አይሆንም? ደግሞ ሰው አትመርጪም እንዳትለኝ! ”

“ አልልሽም! ሰው አትመርጪም የምልሽ ከዚህም ከዚያም ብትይ እንጂ ድሃ ብትወጂ አይደለም።”

“ አዎ ግን ምን መሰለህ? ስወድ እመለከታለሁ።ይህ ሰው ብወልድለት ዘር ያበላሻል አያበላሽም? እላለሁ።አቋሙና መልኩ ካረካኝ እወደዋለሁ፤የጸባዩ ነገር ሳይረሳ።”

 

ሀሳቧን አልተቃወመም።ሆኖም አንድ ትንሽ ቅር ያሰኘው ነገር ነበር። ከሰው ትግባባለች።የመግባባት ችሎታዋን ግን አላደነቀውም።ድርቅ ብላ ትቀርባለች።ካገኘችው ሰው ብትግባባም ቅሉ ይበልጥ የምትፈቅደው ግን የመልከ-መልካሞቹን ዝምድና ነበር።በሆስፒታል በቆየችባቸው 29 ቀናት ውስጥ አስናቀ ብዙ ታዝቧል።ከደማሙ ዘበኛ ጀምሮ እስከ መልከመልካሙ አስታማሚ ድረስ ተግባብታለች።እስከ መልከመልካሙ የጽዳት ሰራተኛ ድረስ ተዋውቃለች።አዛኝ ነች፤ይህ የታወቀ ነው።እና ያን ቁመናና መልክ ይዞ በር በመጠበቁ፤ያኛው ደግሞ ያን ወጣትነት፣ቁመናና መልክ ይዞ ቤት በመጥረጉ አዝና ነው የምትጠጋው? አስናቀ መልስ አላገኘም።

 

“ እስቲ አዜቢና…” አስናቀ ቀለደ “ እኔ ከየትኞቹ እመደባለሁ? ”

“ ውይ!” አለችና ሳቀች “ አንተ ምንም አይወጣልህም አስናቅዬ…ብቻ ትንሽ…እንዲያው ላመል ረዘም ብትልልኝ…” ተንጠራርታ ጭኑን ቆነጠጠችው።

 

“ እስቲ አስናቅ አንድ ነገር ልንገርህ!” አለች ቆይታ፤የተላጠ ስኳር ድንች የሚመስል ጉም የተጋገረበትን ሰማይ ለአጭር ቅጽበት በአይኖቿ ገረፍረፍ አድርጋ “ ለምሳሌ በመጪው አመት አንተ ዩኒቨርሲቲ ግባ፤እኔ ደግሞ ከቤተሰብ ጣጣ ለማምለጥም ይሁን በሌላ ምክንያት የዛሬ ሳምንት ላግባ።ልብስህን ከካልሲ ጀምሮ እኔ ልግዛልህ፤እኔው ጋር ይታጠብልህ።በሳምንት አንድ ቀን እየጠፋሁ አንተ ጋር ልምጣ፤ልጅ ከባለቤቴ አልውለድ።እ?..እና አንተ ከዩኒቨርሲቲ ስትመረቅ ባሌን ፈትቼ አንተን ላግባ።እንዲህ ቢሆን በኔ ላይ እምነት አይኖርህም? ”

“ ሊኖረኝ ይችላል፤ግን ጥልቅ ውይይት ያሻዋል! ”

“ ውይ እኔ ብሆን ግን በደንብ ነበር የማምነው! ”

ብቻ አስናቀ አዜብን አልነበረም።ሃሳቧን የተቀበለው በጥርጣሬ፣በድብቅ ፌዝ እና በግርምት ነበር።እሷ ወደ ማርጀቱ ባይሆንም ወደ መጎልመሱ፤ረጃጅም የትዳርና የወሲብ አመታትን አልፋ።እሱ ከጥሬ ጎረምሳነት ወደ ብስል ወጣትነት፤በእሷው በአዜብ ብቻ ተወስኖ።አዜብ ራስ ወዳድ አፍቃሪ ሆነችበት። በአንድ ነገር ግን ተደሰተ፤ከቀን ወደቀን የአዜብን ባህሪ ገጾች አንድ ባንድ እየገለጠ ነበር።አዜብ ምናልባትም የወጣት ትኩስ ደሙ ማብረጃ ብቻ እንጂ የወደፊት የህይወት ጓደኛው ልትሆን ያለመቻሏ ሃሳብ ከድብርት ጋር ሰረጸበት።

 

ያን ዕለት ማታ ዘውዱ ቤት እንዲጠብቃት ነገረችው።እሱ ይዟት እንዲወጣ ሃሳብ ቢያቀርብም በጄ አላለችውም።ህመሟ በጣም ተሽሏታል።እና ማታ በአንድ ሰዓት የክረምቱን ብርድ ለማባረር ከሰል በምድጃ ሞልቶ አያይዞ ጠበቃት።መጣች።ለረጅም ጊዜ ተጠፋፍተው የቆዩ፣ገላ ለገላ የተዋወቁ  ወጣት ፍቅረኞች እንደሚያደርጉት ሁሉ እንዴት እንደተቃቀፉ አላወቁትም።መብራቱ ጠፍቶ ሲበራ ቦግ ብሎ ነዶ የነበረው እሳት ጠፍቶ አመድ ሆኖ ነበር።እንደገና ለማንደድ የተቸገሩት፣ስለቤት ወጪ አንስተው የተጨዋወቱት፣ከጆንያው ኮርኒስና ከደብዛዛው ሃያ አምስት ሻማ አምፑል ስር ሆነው ያሳለፉት አጭር ምሽት አስናቀ ልብ ውስጥ እንደገና ርህራሄ፣እንደገና ፍቅር ሲጭርበት ተሰማው።በማግስቱ ደግሞ ገና በረፋዱ ተያይዘው ከሆስፒታል ወጥተው የዘውዱ ቤት ተቆልፎ በማግኘታቸው መንገድ ዳር ሆነው የጠበቁት፣የጎሪጥ እያዩዋቸው ያለፉት መንገደኞች፡ቀዝቀዝ ያለው ረፋድ እና በልቡ ውስጥ እንደገና እምቡር እምቡር ይል የነበረው የፍቅር ስሜት አሁን ድረስ ይታወሱታል።

 

***

ህመሟ ስለተሻላት ነግ ከነግ ወዲያ እንደምትወጣ ነገረችው።ሃያ ሰባተኛው ቀን መሆኑ ነበር።ከቀኑ ወደ አራት ሰዓት ገደማ ጉርምርምታና ብልጭልጭታ አስቀድሞ ዝናብ ሊዘንብ ይዘጋጃል።ጭጋግ በጥቅል በጥቅል ሆኖ ሰማዩ ስር ይንጎማለላል።ከዝናቡ ለማምለጥ በመሮጧ ትንፋሿ ቁርጥ ቁርጥ እያለች አንዲት ወጣት ሴት ገባች።የአዜብ ጓደኛ መሆኗ ነው።

“ ምነው ዛሬ በጧቱ? ” አለቻት አዜብ ተገርማ።

“ ዛሬ ስራ አልገባሁም።ክሊኒክ ቆይቼ መምጣቴ ነው። ”

“ ምነው ምን ሆንሽ? ”

“ያው ጨጓራዬ ነው እባክሽ!ወይ ቆርጠው ካላወጡልኝ ወይ ዶሮ መብላት ካላቆምኩ!”

“ አሁን መድሃኒቱን አገኘሽ? ” አዜብ አቋረጠቻት።

“ አንድ ኪሎ ምክርና ሃያ ግራም ታጋሜት…” ሳቀች “ አንቺስ እንዴት ነሽ? ”

“ ከነገወዲያ ሳልወጣ አልቀርም። ”

“ ውይ አሁን እኮ መንገድ ላይ ባለቤትሽን አግኝቼው ሰሞኑን ትወጣለች ብሎኝ ነበር!”

አስናቀ በቅጽበት አይኖቹ ወደ አዜብ ተወረወሩ።ፊቷ ላይ የታየው መረበሽ አስደንጋጭ ነበር።

“ እ!? ” ብላ ጠየቀች።ጥያቄ አልነበረም፤ማቃሰት ነበር።

ጓደኛዋ የአዜብን ሽብር ሳታጤን “ እንዲያውም ወደ አንቺ እንደምሄድ ስነግረው አሁን እንደሚከተለኝ ነግሮኛል።” ስትል ቀጠለች።

አዜብ ወዲያው  ራሷን ተቆጣጥራ በተስተካከለ ድምፅ “ ስራ አልገባም ማለት ነው?” ስትል አስናቀ አደነቃት።አይኖቹ ግን ደም ለብሰው ይከታተሏት ነበር።ልቡ ውስጥ ቋጥኝ እንደተቀመጠ ሁሉ ከበደው።በልቡ ክፍልፋይ ግን የቀናት ክትትሉ ያልታሰበ ውጤት ስላመጣለት በስቃይ የታጀበ እርካታ ብጤ ተሰማው።ምንም ሳይናገር ጥሏት ሊሄድ ዳዳው፤ሆኖም አዜብ ያታለለችውን ባሏን ማየት ጓጓ።

 

በተከተሉት ጥቂት ቅጽበታት የፍቅረኛውን የቸልታ መልስና የባልንጀራዋን ያላቋረጠ ወሬ ሳያዳምጥ እየሰማ እስከዛሬ ባለቤትዮውን እንዴት ሳያገኘው እንደቀረ ሲያሰላስል ቆይቶ ድንገት መልሱ ተገለጠለት።አዜብ ከሰዓት በኋላ ወደ አስር ሰዓት ግድም ሁሌ ራሷን ያማታል፤እና አስናቀ እንዲሄድ ትገፋፋዋለች።ያኔ የባሏ መምጫ ጊዜ ነው ማለት ነው።ምናልባትም ልክ እሱ እንደመጣ ራስ ምታቷ ይተዋታል።

 

ዛሬ!ድና ልትወጣ ሁለት ቀናት ብቻ ሲቀራት…ባለመታደል ይቺን ጓደኛዋን ጣለባት!ጣለለት!ወይስ ላስናቀም ቢሆን ጥሎሽ ነበር?! ዝናቡ የምሩን መውረድ ሲጀምር አስናቀ በመስኮት ተመለከተ።ከጥቂት ደቂቆች በኋላ ደግሞ አንድ የተደላደለ ሰውነት ያለው ረጅም፣ቀይ ሰው በበሩ ሲገባ አየ።ነጣ ያለ ሱሪ፣ጥቁር ኮትና ዝንጉርጉር ሸሚዝ ለብሶ ነጭ ከረባት አስሯል።ከሰላሳ አምስት አመት አይዘልም።ጥቁር አይኖቹ ከተጋደመችው አዜብ ጀምሮ የተቀመጡትን ጠያቂዎች በቅዝቃዜ አዳረሷቸውና ቶሎ ተሰበሩ።አስናቀ ብድግ ብሎ በአክብሮት ሰላምታ ሰጠ።ቁመቱ ከሰውዬው ትከሻ ትንሽ ከፍ ይላል።

 

“ እንዳልኩሽ ደረስኩብሽ አይደል? ” አላት ወጣቷን ሴት በፈገግታ

“ በትክክል!” ከት ብላ ሳቀች።

 

ይቺ ልጅ እውነት ጨጓራዋን አሟታል ? አስናቀ ተገረመ።

 

አዜብ ፍዝዝ ብላ ነበር።ባለቤቷ አልፎ አልፎ አየት ያደርጋታል፤እና ያፍቃሪ ሰው አስተያየት ነበረ።ከአዜብ ጋር ብዙም አልተጨዋወቱ፤ከጓደኛዋ ጋር እንጂ።አስናቀ ብዙም ሳይናገር አንገቱን ሰብሮ እየተቅለሰለሰ ሰውዬውን በደንብ አጠናው።መሳቅ አያበዛም።ሲናገር ቀስ ብሎ ሲሆን ድምጹ ግን ጎርናና ነው።በሚናገርበት ጊዜ ትናንሽ ጥቋቁር አይኖቹ ሰውን ትክ ብው አያዩም።ወዲያና ወዲህ ይራወጣሉ።ሲያወሩለትም ትኩር ብሎ መመልከት አይሆንለትም።መጠየቅ አያዘወትርም።አስናቀ ወሬ ማቋረጥ የማትችለውን የአዜብን ባልንጀራ ጨዋታ እያዳመጠ የፍቅረኛውን የተከዘ ፊትና የባላቤቷን የደስደስ ያለው ገጽታ ተራ በተራ ተመለከተ።አዜቢና እኔ ከሱ በምን ተሽዬ ይሆን የተጠጋሽኝ? ብሎ በልቡ እየጠየቀ ህይወት ከሷ ጋር ያስተዋወቀችው አንድ ተጨማሪ ትምህርት ልታስተምረው መሆኑን ይበልጥ ተረዳ፣ እንደ ማክሲም ጎርኪ።

 

 

 

 

– 5 –

 

ወደ ምዕራብ ጎሬዋ የምትገሰግሰው ፀሃይ ደም መሳይ ጨረሮች ግርጫማውን ሰማይ አቅልመውታል።በጥቂት ሰከንዶች ልዩነት እያረፈ ሽው የሚለው ነፋስ በተሸከመው ብርድ ሰውነትን ውግት ያደርጋል።ጥቂት ቆይቶ የፀሀይ ደም መሳይ ጨረሮች በጭኮላ እያፈገፈጉ፣ የጨለማው ክብደት እያየለ መጀመሪያ በዝግታ በኋላ ግን በፍጥነት ጠይም መልኩ ምድሪቱን እያጥለቀለቀ መጣ።አንዴ የወርቅማ ብርሃን መናኸሪያ የነበረችውን ክፍለ-ፕላኔት ጨረቃ-የለሽ፣ ኮከብ-አልባ ማታ ተጫጫናት።ቀስ በቀስ ጨለማውን ተከትሎ ጉርምርምታ ተሰማ።ጥቅጥቁን ጨለማ አልፎ አልፎ እንደእባብ የሚጥመለመል ብልጭታ መሃል ለመሃል ይቀደውና- ተመልሶ ሊጠፋ – ለቅጽበት ያህል ብቻ ደማቅ ብርማ ብርሃን ያጎናጽፈዋል።

 

በዚህ ማታ የጨረቃም ሆነ የከዋክብት ብርሃን እንደተለመደው ድምቀት አልሰጡም።በየመንገዱ የተዘረጉት ሰው-ሰራሽ አምፑሎች ብቻ ሰው-ሰራሽ ድምቀት ለግሰዋል።በየደቂቃው ብልጭ የሚለው ጥምዝምዝ ብርሃን በእድሜው ማጠር የሚያበሳጭ ነበር፤አጉል ተስፋ፣የውሸት ደስታ የሚሰጥ አይነት እንጂ ቋሚነት አልነበረውምና!ወይስ በማስደንገጡ ነበር የሚያበሳጨው?!

 

ያን ዕለት ማታ የአስናቀም ሰውነት በጨለማ የተሞላ ነበር።ጨለማው ከትልቅ ጭንቅላቱ አንስቶ እስከእግር ጥፍሩ ድረስ ይዞታል።አንዴ ጨጓራው ውስጥ ብቻ ይቆለላል- ቅጥል! አንዴ ደረቱ ውስጥ- እፍን! አንዴ ጭንቅላቱ ውስጥ- ጭንቅ! በሌላ ቅጽበት ደግሞ ስስት ይልና በመላ አካሉ ይበተናል-ዝግንን! ይህ ጽልመት በቅዝቃዜው የሚወጋ፣በፍላቱ የሚፈጅ፣በስለቱ የሚቆርጥ ነበር።

 

የመኝታ ቤቱን ትንሽ መስኮት ከፍቶ ጨለማው ላይ አይኖቹን ተከለ።ዝናብ መጣል ጀምሯል።ውሽንፍሩ አልተሰማውም።በብልጭታው መሃል የሚታየው ገዳዳ የዝናብ አወራረድ አልታየውም።ሀሳቡ ርቆ ሄዷል።ያቺ ልጅ-ያቺ ቀጠን አጠር ያለች ቀይዳማ ልጅ ጋር ነጉዷል።ጥቁሩን ጨለማ እየሰነጣጠቀች፣የሰማዩ ነጎድጓድ ሳያስደነብራት፣ብልጭታው ሳያስደነግጣት፣ነጠብጣቡ ሳይሰማት፣ ዳለቻ ቀሚሷን ለብሳ፣ቡናማ ዳርቻ ያለውን መነጽሯን ሰክታ እዚያው ዝናቡ ውስጥ ፊት ለፊቱ ተገተረች።

 

“አዜብ!” አላት “ ወይ! ” አላለችውም።አንደበቷ ሳይንቀሳቀስ “ እሺ፣ የምትለውን እሰማለሁ!” እንደምትል ሁሉ በፀጥታ ጠበቀችው። “ አዜብ ለመሆኑ እኔን ነው ባልሽን ያታለልሽው? ትዳር እያለሽ ከኔ ጋር ኮስተር ያለ ፍቅር የጀመርሽበት ምክንያት ከቶ ምን ይሆን? በተፈጥሮ ሁሉ የሚያምርሽ ሆነሽ ነው ወይስ ካገባሽው ሰው ጋር ባለመፋቀርሽ? እስቲ ንገሪኝ በናትሽ! ” ውሽንፍሩ ከጎፈሬው ጀምሮ ደረቱን አረስርሶታል።እሷማ ጭራሱኑ ስለ ዝናቡ የምታስብም አትመስል “ በውነቱ ዕንቆቅልሽ ነው የሆንሽብኝ! መልክሽ የየዋህ ነው።ግን በዚህ የየዋህነት ጭንብልሽ ስር እውነተኛው አንቺነትሽ ተደብቋል።የምታሳያቸው የቅንነት ትዕይንቶች ሁሉ አውቀሽ ለመወደድና ለመደነቅ ስትይ የምትሰሪያቸው ውሸቶች ናቸው።አዜብ ለመምሰል እንደምትሞክሪው ንፁህ አፍቃሪ አይደለሽም።የህይወት ነጋዴ ነሽ።በህይወት ከሚያጋጥሙሽ ደንበኞችሽ ጋር ለመደሰት ሁሌም ዝግጁ ትመስዪኛለሽ።ገንዘብ ወዳድ ነሽ ማለቴ አይደለም።ግን ብዙ ሰው ያምርሻል!ወንድ ያጓጓሻል!”

 

አይኖቹን ህይወት ከማይነበብባቸው አይኖቿ ላይ አልነቀለም።በቆመችበት ቁራጭ መሬት ላይ የተተከለች ይመስል ወዲያ ወዲሀ ሳትል ግትር ብላ ቀረች።አስናቀ ቢናገርም እሷ ጭንብል ያጠለቀች ይመስል የፊት ገጿ አይቀያየርም።

 

“  ወድጄሽ ነበር!በእውነቱ ለአንቺ ያለኝ ፍቅር አሁንም ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ማለቴ አይደለም!ግን እንቅሻለሁ። አዜብ ሳፈቅርሽ ከኔ በዕድሜ፣በሀብት፣በትምህርት ደረጃም ቢሆን እንደምትበልጪኝ እያወቅሁ ነው።ይህ ለግንኙነታችን እንቅፋት ይሆናል ብዬ ገምቼ ነበር።ግን አንቺ ቅን ነበርሽ፤አፍቃሪ ነበርሽ፤ትሁት ነበርሽ።እና የራሴን ያህል ወደድኩሽ። አሁን ግን ይብቃን…” ንግግሩን አልጨረሰም፤ከቤቱ ወዲያ ማዶ በግንብ ታጥሮ የተኮፈሰው ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ዛፍ መብረቅ ሲጥለው ከማታ ሰመመኑ ብንን አለ።መስኮቱ ላይ የተደገፈው ክንዱ ደንዝዟል።ወደ መኝታ ቤቱ ውስጥ ተመለከተ።የእሱና የታናሽ ወንድሙ አልጋዎች፣መፅሃፍ መደርደሪያው ከነመፅሃፍቱ፣ጠረጴዛና ወንበሮቹ በትዝብት ይመለከቱታል።

 

የራሰ ስውነቱን የሚያዳርቅበት ፎጣ ፍለጋ ከመሄዱ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ውካታማው ጨለማ ፊቱን አዞረ።አዜብ የለችም።የእሷ ሁለት ቅርጻም እግሮች ቆመውበት የነበረው  ቁራጭ መሬት በውሃ ተሸፍኗል።መራር ሳቅ ስቆ መስኮቱን ጥርቅም አድርጎ ዘጋና ሰውነቱን አደራርቆ፣ፒጃማውን ለበሰና አልጋው ላይ በጀርባው ተንጋለለ።የአዜብ መልክ ሃሳቡን ማባረሩን አላቆመም።ቅናት በሹል ጦሩ ይሸቀሽቀው ነበር።ንቀቱንና ንዴቱን አሸንፈው ከአዜብ ጋር ያሳለፋቸው የፍቅር ቅጽበታት ህሊናውን ሸንቁረው እየገቡ ረፍት ነሱት።ያ እሱን አንዴ በፍቅርና በስስት ያቀፈው ክንድ በሌላ ሰው አንገት ላይ የመጠምጠሙ ሃሳብ ዘገነነው።ምናለ አዜብ ከዚህ ያነሰች አፍቃሪ፣ከዚህ ያነሰች ለስላሳ፣ከዚህ ያነሰች ትኩስ ብትሆን ኖሮ?

 

ለመጀመሪያ ጊዜ ቅናት የጀመረው መቼ እንደሆነ ሲያስብ አስናቀ ከዚህ በፊት ያወቃቸውን ልጃገረዶች ድንገት አንድ በአንድ ያስታውስ ጀመር።አእምሮው መጽናኛ እየፈለገለት ይሁን ማባባሻ እሱም አልተረዳው።የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ የነበረበት ዓመት ሙናዬን ይዞ ብቅ አለ።ጠይም መልኳ፣ዘለግ ደልደል ያለ አቋሟ፣ትናንሽ አይኖቿና ጠባብ አፏ ከአጭር አፍንጫዋና ከአጭር ሉጫ ጸጉሯ ጋር ብቅ አሉበት።ራንግለር ሱሪዋን ለብሳ ባይኑ ላይ ብዥ ብዥ አለችበት።አብሮ አደጎች ናቸው።ድሮ የቅጠል እንጀራ እየቀጠፉ፣የጭቃ ዳቦ እየጠፈጠፉ፣የአፈር ወጥ እየሰሩ፣ ባልና ሚስት ባልና ሚስት እየተባባሉ ሲጫወቱ ነበር ያደጉት።ለእነ አስናቀ ጎረቤት ከሆኑት ከሚያሳድሯት አያቶቿ ቤት ወጥታ ወደ ወላጆቿ ቤት ከሄደች ውሎ አድሮ ነበር።ከጥቂት አመታት በኋላ አድጋ ተመለሰች።ያኔ ነው አስናቀና እሷ የተወዳጁት።እውነቱን ለመናገር አስናቀ ፍላጎት ብቻ እንጂ ፍቅር ጨርሶ አልነበረውም።እሷም ፍቅር ያደረባት አትመስልም።ግን ሁለቱም ትኩስ የወጣት ገላዎቻቸውን አነካክተዋል።ይህ ከሆነ በኋላ ሙናዬ ከቤት እየጠፋች መንቀዋለል ጀመረች።ከብዙ ወንዶች ልጆች ጋር ታየች።ብዙ አልቆየም፤አንዲት ሴት ልጅ ወለደችና ከአዲስ አበባ ተሰወረች።ድሬዳዋ ሴትኛ አዳሪ ሆናለች ይባላል።

 

ሶፊያ ድንገት ድቅን አለች።ቀጭን ስጋማ ሰውነቷ በቀይ መልኳ ላይ ተሰክተው የሚንከራተቱት ጥቋቁር አይኖቿ፣ሳቂታ ገጽታዋና ቢጫ ጥርሶቿ አመታቱን አቋርጠው ከተፍ አሉበት።ጥልቅ ፍቅርም ባይሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የፍቅር ጨረፍታ የነካው ከእሷ ነበር።የክብ ክንዷ ስሜታዊ አስተቃቀፍ ገና ምንም የማያውቀው ቅን ልቡን በጥንካሬው አጨማደደው።ሶፊያ ከእሱ ጋር  ያን ፈጽማ ከሌሎች ልጆች ጋር ሲያያት ያኔ ቅናት ጀመረው።ነገር ግን በኋለኛው  የወጣትነት ዘመኑ እንዳደረገው አልተጨቃጨቀም ነበር።ቅናቱንም ንዴቱንም በሆዱ አምቆ ከስሜቱ ጋር እየታገለ ቀስ በቀስ ራቃት።እንደ ማታ ፀሀይ እያፈገፈገ…እያፈገፈገ…ሲርቃት ይረሳኛል ብሎ ያላሰበው ፍቅር ተረስቶት በምትኩ አንዴ የፍቅር አምሳያ መስሎ የታየው የሶፊያ ቆንጆ ፊት የቅብዝብዝነት አምሳያ ሆነበት።

 

ንቅሳታም ጥርሶቿ በፈገግታ ተገልጠው፤ቀይዳማ፣ ቆንጆና ማራኪ ገጽታዋ እንደፀሀይ እያብረቀረቀ ዕንቁ መጣች።የብልህ፣የትሁትና የጸባየ ሸጋ ልጃገረዶች ምሳሌ ነበረች።አስናቀ እሷን ሲያስታውስ ናፍቆትና ምኞት ሁልጊዜ ጠቅ ያደርጉታል።አዜብና ወይነ-ጠጅ አበባ እንደማይነጣጠሉ ሁሉ ዕንቁና የመስፍን አበበ “ትዝታ” የማይነጣጠሉ ናቸው።

 

በፍቅርሽ ትዝታ ልቤ ተሸፍኖ፤

                   መውጫ ይፈልጋል እንዳበደ ሆኖ።

 

በዘፈኑ የተለየ ነገር አይቶበት አይደለም።ነገር ግን ዜማውን እያዳመጡ የተቀመጡበት አጭር ቅጽበት የዘለአለምነትን ያህል አይረሳውም።እንደእውነቱ ከሆነ ከእንቁ ጋር ያሳለፉት ጊዜ በጣም አጭር ነው።በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ከጥቂት ቀናት የከንፈር ንጥቂያ ያለፈ አልዘለሉም።ሆኖም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰውን መገመት ከተቻለ ዕንቁ ለአስናቀ እውነትም ዕንቁ ነበረች።ስለማህበራዊ ኑሮ ያላት አስተያት፣ለትምህርት ጉጉነቷ፣ለመጽሃፍት ያላት ፍቅር በወጣቱ አእምሮ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይዘው ቀርተዋል።የወደዱት ነገር ሁሌም ውድ ነውና ፍቅሩን እንዳይጨርስ በራሳቸው መንገድ ወላጆቿ እንቅፋት ሆኑ።ዕንቁን ክፍለ ሀገር ላኳትና እዚያው አስቀሯት።ከዚያ በኋላ ለመንፈቅ ያህል አስናቀ ሲባንን ነበር።ምግብና ውሃ ጠላቶቹ የሆኑ ያህል ርቋቸው አዛኝ እናቱን አሳስቧቸው ከርሟል።እሷን ፍለጋ ወደሄደችበት ክፍለ ሀገር ለመሄድ አንድ ሁለቴ ቢሞክርም አልተሳካለትም።ከዚያ በኋላማ ትዝታዋ ከወራቱ ጋር እየነጎደ…እየጠፋ…እየከሰመ…ከአእምሮው የትዝታ ሰሌዳ  ጨርሶ ባይፋቅም ደበዘዘ።

 

በንፅፅር ለረጅም ጊዜ አብሯት የቆየውና ትዝታዋ አሁንም ገና ያልጠፋው ቆንጆ ትንሽ ልጃገረድ ታወሰችው-ራሄል።ይህችን ልጅና አዜብን አወዳደራቸው።አዜብ በማስተዋል ከራሄል በላይ፤በቁንጅና ከራሄል በታች።በፍቅር አዋቂነት ከራሄል በላይ።አስናቀ የረጅም ጊዜ ፍቅርን ያገኘው ከራሄል ነበር።በቀን በቀን እየመጣች አብረው ያሳለፏቸው የተቀደሱ ቀናት በትዝታ ጦራቸው ይወጉታል።ወረቷ ስላለቀላት ይሁን ሳያውቅ አስቀይሟት የቀረችው እሷው ነበረች።ሊመልሳት ቢሞክርም ስላንገራገረች እርግፍ አድርጎ ትቷታል።ነገር ግን አሁንም ቢሆን በራሄል ላይ የጥላቻ ስሜት የለውም።

 

ሌሊት እንደተኛ ወደታች የተበጠረ ፀጉሯን በላስቲክ ቋጥራ፣የምታዘወትረውን ነጭ ረጅም ቀሚሷን አጥልቃ፣ ጃኬት ደረብ አድርጋ፣ስስ ከንፈሮቿ ፈገግ ብለው፣ቲማቲም የሚመስሉት የጉንጭ አጥንቶቿ ስጋ ይበልጥ ደም መስለው አንዳንዴ በህልሙ ብቅ ስትልበት ይነቃና “ አይ አንቺ ትንሽ ቆንጅዬ እባክሽ ልተኛበት።ሌላ ካገኘሁ እኮ ሰነበትኩ። አንቺም ሸጋውን ያጋጥምሽ! ” ብሎ ፈገግ ይልና ወደ እንቅልፍ አለም ዳግም ይነጉዳል።

 

– 6 –

 

ዘውዱ አዜብ ስልክ ደውላ እንደነበርና እሁድ ጧት በሶስት ሰዓት ስለምትመጣ ጠብቀኝ ማለቷን ለአስናቀ ነገረው።ከሆስፒታል ከወጣች ሁለት ሳምንት አልፏት ነበር።አስናቀ አታላይ ፈገግታዋን ከትዝታው ለመፋቅ ታገለ እንጂ አንዴም ስልክ አልደወለላትም።ደውሎ ከቀጠራት በኋላ የፈጸመችውን የክህደትና የማታለል ወንጀል ፊት ለፊት ነግሯት ለመለያየት ያሰበበት ጊዜ ነበር።ወይም ደግሞ አስከዛሬ ላሳለፉት መልካም ጊዜ ሲባል በሰላም አነጋግሯት ፣በለስላሳ አንደበት ጥፋቷን አስረድቷት ከአሁን ወዲያ እህትና ወንድም እንዲሆኑ ሀሳብ ለማቅረብም ከጅሎት ነበር።

 

ይሁን እንጂ የአታላይ ምላሷን አስማት፣የተለማማጭ አንደበቷን ስለት፣የከብላላ አይኖቿን ጦርነት ማሸነፍ አለማሸነፉ አጠራጠረው።ለሷ ያለው ፍቅር አንዳንዴ በጥላቻና በፅያፌ፣አንዳንዴም በቅናትና በንዴት ይበረዝ እንጂ ሰንኮፉ ገና ከልቡ ያልወጣ መሆኑን ያውቃል።ስለዚህ በጊዜ ለመጠቀም ወሰነ።ጊዜ የማይሽረው ነገር የለም።የጊዜ ርዝመት የህሊና ቁስልን ሲያሽር ሰምቷልም ተመልክቷልም ።እና አስራ አምሰት ቀን ሙሉ የእሷን ገጽታ ከትውስት ማህደሩ ውስጥ ለማውጣት ታገለ።ትግሉ ፍሬ አልባ አልሆነም።ድሮ በቀን ቁጥር-የለሽ ጊዜ የሚያስታውሳት አዜብ አሁን አልፎ አልፎ እንጂ ገጽታዋ ብቅ ማለቱን አቆመ።ትልቅ ሰላማዊ ረፍት ሆኖ ተሰማው።ታዲያ አሁን…

 

“ እንዴት? መቼ ደወለች እባክህ?! ”

“ ዛሬ ነው የደወለችው።ለእሁድ ቀጥራሃለች፣እዚያው እኔው ቤት። ”

 

ለአንድ አፍታ አይኖቹን ቦዘዝ አደረገ።ድምጿ ታወሰው፣ያ እንደምንጭ ውሃ ኮለለለል…እያለ የሚወርደው ድምጿ!ያ ያለምንም እንቅፋት ጉሮሮዋን እየገመሰ የሚንበለበለው ወጣት ድምጿ! ሳይፈቅድ የድሮው ስሜቱ ላንድ አፍታ እንደገና ተመለሰበት።መረሳት የጀመረው መልክ እንደገና ቦግ ብሎ ተጋረጠበት።መቀዝቀዝ የጀመረው ተኩሳታዊ ስሜት አሁንም መላ አካላቱን ሲያቃጥለው አስናቀ ደሙ ፈላ።አልቆየም ወዲያውኑ ዝናቡ፣የሆስፒታሉ ክፍል፣የአዜብ ጓደኛ፣ባለቤቷ፣በጭንቅ የተንከራተቱት የአዜብ አይኖች በነጭ አቡጀዲ ላይ እንደሚታይ ተንቀሳቃሽ ስዕል ህያው መስለው ታዩት።

 

የወረረው ትዝታዊ የፍቅር ስሜት በተራው ከሁለት ሳምንታት ወዲህ ላደረበት ስሜት ቀስ በቀስ ቦታውን እየለቀቀ ሄደ።ለአንድ አፍታ ውጦት የነበረው የስሜት ማዕበል በላዩ ላይ የሚነፍሰው ነፋስ ጋብ እንዳለለለት ባህር  ተግ ረጋ አለለት። ረጋ አለ እንጂ ጨርሶ አልቆመም።

 

ለረጅም ጊዜ የአስናቀን የሚለዋወጥ ፊት በተገርሞ ሲያስተውል የቆየው ዘውዱ “ አስናቀ ምን ነካህ? ” ሲል ጠየቀ።

“ ምንም…ምንም!” አለና  መለሰ አስናቀ እየተቻኮለ “ ጥሩ በቃ እሁድ እንጠብቃታለን ዜድ ”

 

አስናቀ ከዘውዱ ከተለየ በኋላ ወደቤቱ አልገባም።ከጓደኛው ጋር ከመገናኘቱ በፊት ልማደኛ የቀን እንቅልፉን ከተወጣ በኋላ ትንሽ ለማንበብ ሀሳብ ነበረው።አሁን ግን ለመተኛትም ሆነ ለመቀመጥ፣ለማንበብም ሆነ ለመስማት ምንም ዝንባሌ አልነበረውም።ጨብጦት የነበረው ድካምና እንቅልፍ እንደበጋ ደመና ተበትኗል።የመንገዱን ጭርታ በመምረጡ ቁልቁል ወደ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል አቅጣጫ ወረደ፣እያሰላሰለ፣እያስተነተነ።

 

ለምናባቷ ነው የምትፈልገኝ?  ብሎ ራሱን ጠየቀ።አሁንም ራሱን ደግሞ ጠየቀ።ሌላ ሀሳብ ማፍለቅ የማይችል ይመስል ይኸው ጥያቄ ብቻ እየተደጋገመ ይደውልበት ጀመር።አንዴ እያጓራ በሚሄድ የጭነት መኪና ድምጽና ጭስ፣አንዴ በሚያነጓው እንቅፋት ከቀን እንቅልፉ ብንን ይላል።ለጥቂት ጊዜ አእምሮው አካባቢው ባሉት ነገሮች ያተኩራል።ለቅጽበት ያህል ደግሞ እንዲያው ባዶ ይሆናል።ትንሽ ይቆይና ሀሳቡ ሁሉ የተዘበራረቀ ይሆንበታል።ወዲያው ብዙ ሀሳቦች ድንገት ጥልቅ ይሉበትና አእምሮውን ያጨናንቁታል።በእንዲህ አይነት ተጉዞ ህንጻ ኮሌጅ በር ጋር ሲደርስ ነበር የአዜብ ፍቅር የፈጠረው ስሜት እየተጫነው  ለምናባቷ ይሆን የፈለገችኝ?  የሚለውን ጥያቄ መልሶ መላልሶ መደጋገም ብቻ ሳይሆን እያስተነተነ ለመመለስ የሞከረው።

 

መጀመሪያ ያ ከልብ የመጣ የሚመስለው ሰፊ ፈገግታዋ ድቅን አለበት።በቀላሉ ከአንደበቷ የሚወጡት የማሞካሻ ቃላት ተሰሙት።የተቆጣን ሰው ከመቅጽበት የምታበርድበት ተማጻኝ ጸባይዋ ታሰበው።ሴትነቷ፣በአንገቱ፣በጀርባው፣በወገቡ ዙሪያ የሚጠመጠሙት ቀጫጭን ክብ ክንዶቿ፤ከናፍሩን ካሉበት ፈልገው ለመመጥመጥ፣ለመጉረስ የሚንከራተቱት ከንፈሮቿ ታሰቡት።አለያም አሁንም ሰውነቱ ላይ ያረፉ ይመስል ዳሰሱት።የፍቅር ሽርፍራፊ ተሰማው።

 

“ ግን እኮ ደህና ልጅ ነበረች!” አለ ለራሱ።ወዲያው ግን ይህ ሁሉ የሱ፣ያስናቀ የብቻው አለመሆኑ ድንገት ብልጭ አለበትና የተሰማውን የፍቅር ሽርፍራፊ የበለጠ ሸራረፈው።አታላይነቷ ከሁሉ በላይ ነገሰና አይኑን አፍጥጦ ተጠጋው።ደማም ማራኪ መልኳ እያሾፈ፣እየቀለደ መጣበት።በቡጢ ሊነርተው አለመቻሉ አናደደው።

 

የፈለገችኝ ለምንድነው?

 

“ የድሮውን እናድስ ለማለት?…ያው በዚያ ልስልስ አንደበቷ ልትደልለኝ? ምናልባት እኮ እሷ አታፍርም ባሌ አይደለም ትለኝ ይሆናል!ያም ሆነ ይህ እኔ ከአሁን ወዲያ የሷን እህትነቷን እንጂ ወዳጅነቷን አልሻም!አልሻም!አልሻም! ” ብሎ ጮኸ።ደግነቱ በአካባቢው ሰው አልነበረም።

 

አስናቀ አንድ ጊዜ ከአዜብ ጋር ስለትዳር ሲጨዋወቱ “ ለመሆኑ አዜብ ባል ብታገቢ ምን ያህል ታማኝ ትሆኝለታለሽ ? ” ብሎ በጠየቃት ጊዜ የፊቷ መለዋወጥና አንዴ በማታ ፊልም አይተው ሲመለሱ ያደረባትን የድብርት ስሜት አስታወሰ።

 

ብዙ ተጓዘ።ቀኑ ደንገዝገዝ ማለት ጀምሯል።አስናቀ የመቆምም ሆነ የማረፍ ዝንባሌ አልነበረውም።አየር ጤና ደረሰ።ተስፋ ድርጅትን አለፈ።አንዳንድ የሌሊት ወፎች ዣንጥላ መሳይ ክንፋቸውን ዘርግተው፣የአይጥ መሳይ አፋቸውን አሞጥሙጠው መብረር ጀምረዋል።ባሻገር የአውቶቡስ መቆሚያውን ተመለከተ።ሰዎች አልነበሩበትም።ገና አሁን ቀኑ መምሸቱን ተገነዘበ።በዝግታ የሚያዘግመው ነፋስ ጎፈሬውን እክክ ያደርገዋል።አንዳንዴ በአጠገቡ የሚያልፉት መኪኖች ድምጽ ጆሮውን ይመታዋል።ቀኑም እየጠቆረ…እየጠቆረ…ይሄዳል።የወጣትነት ዘመኑም በሰከንዶች እየተቆጠረ…እየተቆጠረ… አውቶብስ ለመጠበቅ ወደ ማቆሚያው አመራ።

***

እሁድ የደረሰው በቶሎ አልነበረም።አስናቀ ለብቻው የሶስት ቁጥር አውቶብስን መንገድ ተከትሎ ባዘገመበት ወቅት ጊዜው የሮጠውን ያህል እሁድን በፍጥነት ጎትቶ አላመጣውም።ዝግም…ዝግም…ዝግም…ቅዳሜ ምሽት ወደ እሁድ ጧትነት፣እሁድ ጧት ወደ ረፋድነት ተቀየረና አዜብ እመጣለሁ ያለችበት ሰዓት ከተፍ አለ።ለአስናቀ የስቃይ ጊዜ ነበር።ከአዜብ ጋር ልገናኝ አልገናኝ በማለት ሲሟገት ቆይቶ ላለመገናኘት ወስኖ ነበር።ታዲያ አሁን አልጋው ውስጥ ሆኖ ሰዓቱን ተመለከተና አዜብን ዘውዱ ቤት ሆና ላለማሰብ ሞከረ።ነገር ግን እንደተለመደው የዘውዱ አልጋ ጫፍ ላይ ተቀምጣ ትታየው ጀመር።ከአልጋው እመር ብሎ ተነሳና ልብሱን ለባብሶ በታክሲ ወደ ካዛንቺስ በረረ።በተቻለ መጠን አዜብ ትኖራለች ብሎ ከሚያስበው ቦታ ለመራቅ ነበር።እዚያ እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ ከሻይ ቤት ሻይ ቤት እየተንከራተተ ውሎ ወደቤቱ ሲመለስ በድሉ ተደስቶ ነበር።ማታ ዘውዱ አስናቀን ፈልጎ አግኝቶ አዜብ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ስትጠብቀው እንደዋለችና እንባዋን እያዘራች በነገሩ ሁሉ ማዘኗን እንደገለጸች ነገረውና ልቡን አራደው።

 

ሌላ አንድ ሳምንት አለፈ።እሁድ ዕለት።ረፋዱ ላይ።ዘውዱ  መጣና አስናቀን ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው።

 

“ ዜድ ዛሬ በጧት ምን ተገኘ? ”

“ ምን ያልተገኘ ነገር አለ አስናቀ?…ቶሎ ተነስና ወደ ቤት እንሂድ! ”

“ ምንድነው ነገሩ? ደስ ደስ ያለሽ ትመስያለሽ!”

“ እስካሁን ሰላልነገርኩህ ይቅርታ ! ሳይለይለት አልነግርህም ብዬ ነው!አንዲት ቆንጂት አግኝቻለሁ!ሳምንት ይሆነናል።ስላንተ ነግሬያት ካላስተዋወቅኸኝ ብላ ወጥራኛለች።ቶሎበል !እቤት ትቻት ነው የመጣሁት፣ ትቸኩላለች፤አባቷን ሸውዳ ነው የመጣችው!” አጣደፈው።

አስናቀ በደስታና በጉጉት ተወጥሮ ከጓደኛው ጋር ወደ ቤቱ ገሰገሰ።ዘውዱ ቤቱ አጠገብ ያለች ሱቅ ጋር ሲደርሱ “ ቤት ገብተህ ጠብቀኝ፣ለስላሳ ገዝቼ ልምጣ! ” አለና  ወደ ሱቋ አመራ።

 

የአጥፊ ፈገግታ ፊቱ ላይ ያየ መሰለው፤አስናቀ ወደ ጓደኛው ቤት እያመራ።

 

ዳረ-ቡናማ መነጽሯን ሰክታ፣ጸጉሯን አስናቀ እንደሚወድላት ወደታች አበጥራ፣የወየበ ቅጠል የሚመስል ቀሚስና ሰማያዊ ክፍት ሹራብ ደርባ አልጋው ጫፍ ላይ ተቀምጣለች፣አዜብ።አስናቀ አይዩን አላመነም።በሩ ላይ እንደተገተረ ቀረ።ወደኋላው ለመመለስ እየቃጣው የዘውዱ ተንኮል እንደማናደድም፣እንደማሳቅም አለው።

 

“ ምነው ደነገጥክ አስናቅ? ግባ እንጂ!” አለችው ስትፈራ ስትቸር፤ያጥፊ ፈገግታ ፊቷን ሸፍኖታል።

 

ገብቶ ወንበሩ ላይ ተቀመጠ፤ንግግር የለ ፈገግታ።በድንግርግር የተመሉ ቅጽበታት አለፉ።

ላመል ቀና ብሎ ተመለከታት።በጥፋተኝነት ፈገግታ ታርሶ የነበረው ገጽታዋ አሁን ጭስ እንደመታው እቃ ወይም ሳሙና እንደተጋገረበት መስታወት ግርጥት ብሏል።ዓይኖቿ ከቡናማ መነጽሯ ስር ሆነው በቅጡ አይታዩ እንጂ የሚያዩት መሬት መሬቱን ነበር።

 

“ ለመሆኑ ደህና ነህ አስናቅ? ” አለችው እዝን ብላ።መነጽሯን አውልቃ አጠገቧ ከቅርጫቱ ጠረጴዛ ላይ አስቀመጠችው።

“ ምን የምሆን ይመስልሻል? ”

 

አልመለሰችለትም።

 

“ ስለሁሉም ነገር ይቅርታ!” አለችው ቆይታ ቆይታ “ ጥፋተኛዋ እኔ ሳልሆን ህይወት ራሷ ልትሆን ትችላለች!ወይም እድሌ! ነገር ግን ስለ ህይወትም ይሁን ስለ እድሌ ይቅርታ እጠይቃለሁ! ”

 

አስናቀ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀና ብሎ አተኮረባት።አይኖቿ እንባ አላቆረዘዙም።ነገር ግን ጥልቅ ሀዘን አርግዘው ነበር።ይቺ ሴት ማነች? አለ በልቡ፤ሰይጣን ወይስ መልአክ?

“ እኔን ነው ይቅርታ የምትጠይቂው አዜብ? ” አላት በትህትና “ እኔን ምን አደረግሽኝ? የበደልሽው  ባልሽን!”

“ አስናቅዬ እንደምትወደኝ አውቃለሁ።እና ያወቅከውን ነገር ማወቅህ እንደሚጎዳህ ይገባኛል።”

“ ነበር! አሁን ግን ድኛለሁ! ” አላት ጠንክሮ።

“ እኔ ደግሞ ታምሜያለሁ! ” እንደማልቀስ እያላት “ ብታምንም ባታምንም እኔ እወድሃለሁ! ”

 

እንባው መጣበት።ሊመልስላት አልቻለም።ከሆድ ብሶቱ ጎን ንዴትና እልህ ይተናነቀው ነበር።

“ አሁንም ማታለልሽን አታቆሚም? ” ጠየቀ እንደምንም።

 

ለቅጽበት ያህል ፊቷ ተለዋወጠ።አይኖቿ ደብዘዝ ጠበብ አሉ።የፊት ቆዳዋ ሰብሰብ ጨምደድ አለ።

 

“ ያልገባህ ነገር አለ አስናቅዬ!” አንደበቷ ለስላሳና አሳዛኝ ነበረ “ ጥፋቴ ይገባኛል!ምክንያት ግን አለኝ።” ትንሽ እንደማንገራገር አለችና “ አዎ ባል ያገባሁት በፍቅር ስለፍቅር አልነበረም።ከቤተሰቤ ለማምለጥ ነበር።እናትና አባቴ ያሉት ደሴ መሆኑን ታውቃለህ።እኔ እዚህ በወንድሞቼ ነገር መበሳጨቱ ቢሰለቸኝ፣ትዳር ያዝኩ።ባለቤቴ ጨዋ፣የማይጠጣና የማያጨስ፤ከዚያም በላይ ደግሞ በጸባዩ ምቹ፣በጣም ምቹ ነው።እና ትዳር የያዝኩት ምቾት ፍለጋ ነበር፤ማምለጫ።”

 

አስናቀ ላንዳፍታ በሀሳብ ተመሰጠ።አንድ ጊዜ አዜብ ያጫወተችው ትዝ አለው።ከእናት ከአባቷ ጋር አትስማማም።በተለይ እናቷን አትወድም።ጠፍታ አዲስ አበባ ትመጣና አጎቷ ጋር ተቀምጣ ትምህርቷን ትቀጥላለች።ከአጎቷ ሚስት ጋር ባለመስማማቷ ትጠፋና ለሁለት አመታት ያህል የገባችበት ሳይታወቅ ትቆያለች።ትምህርቷን ግን አላቋረጠችም።የት እንደነበረች ለአስናቀም ቢሆን ደብቃዋለች።ዲግሪዋን ከተቀበለች በኋላ ከቤተሰብ ትታረቃለች።

 

“ በትዳር ላይ መወስለት ግን ሀጢያት መሆኑን አታምኚም? ”

“ አትፍረድ ይፈረድብሃል ነው አስናቅዬ!ሳያገቡ ወሲብም ሀጢያት ነው! ”

“ ማለቴ በሃይማኖት በኩል ሳይሆን በህሊና ! ”

“ ነው፣ይገባኛል ግን….”

 

መልስ ጠፋት።እናም መደናገር በፊቷ ላይ ታየ።መነጽሯን ከጠረጴዛው ላይ በደመ-ነፍስ አንስታ አጠለቀችው።ልትሄድ መስሎት ነበር።መልሳ አወለቀችና በእጇ አንጠለጠለችው።

 

“ ባልሽ ይወድሻል? ”

“ የሚወደኝ ይመስለኛል። ”

“ አንቺስ ትወጅዋለሽ? ”

“ ያሳዝነኛል!”

“ ስለሚያሳዝንሽ ነው በላዩ ላይ የምትማግጪው?…ከኔ ሌላ ስንት ወዳጆች አሉሽ ? ” አስናቀ ጥርሱን ነክሶ ጠየቀ።

“ አስናቀ እንደሱ አትበል እባክህ! ” እንባ አነቃት።

“ እና ምን ልበልሽ?! ”

 

የመጀመሪያዎቹ የእንባ ጠብታዎች ዝርግፍ አሉ።አይ ሴቶች!ሲል አሰበ አስናቀ፣ደግነቷ አንዴ ሽው ብሎበት ንዴቱ ተግ፣ልቡ ራራ ሲልበት፤እንባቸው እንዴት ቅርብ ነው? ለደስታ እንባ! ለሀዘን እንባ! ለማታለል እንባ! የሚል ያነበበው የት ነበር? ወይስ የትም አላነበበም?

 

“ አዜብ ይህን የምነግርሽ እንድታለቅሺ አይደለም!”

“ ተወው ተወው አስናቅ!ከዚህም አይብስ! ” አለችና ተንሰቀሰቀች።እየተንከባለለ የሚወርደው ትኩስ እንባዋ ከመታየት ይልቅ ተሰማው።ሳይፈልገው ልቡ በትኩስ እንባዋ እንደጮማ ሲቀልጥ ታወቀው።የሚርገፈገፍ ትከሻዋን ለጥቂት ቅጽበታት ሲታዘብ ቆየና ከመቀመጫው ተነስቶ ጸጉሯን ወደታች ዳበስበስ እያደረገ

“ ይበቃል አዜብ በቃ!” አላት ኮስተር ብሎ ግን በቀስታ።

 

በሁለት እጆቿ ጭኑን ጥፍር አድርጋ ያዘችና ሱሪው ላይ እንባዋን ጠረገችው።ትንሽ ልጅ መሰለችው።ባለበት ተገትሮ ቀረ።ወገቡን ይዛ አጠገቧ እንዲቀመጥ ወደታች ጎተተችው።እሷ እየተነፋረቀች፣እሱ ነፍሱ እየተጨነቀች ፊት ለፊቱ ግርግዳውን እያየ በዝምታ ተቀመጡ።

 

“ እስቲ በፈጠረሽ ከኔ ጋር ባደርሽባቸው ለሊቶች ለባለቤትሽ የሰጠሽው ሰበብ ምን ነበረ? ” ብሎ ጠየቃት ድንገት ዝምታውን ገስሶ።

 

እንባዋን ሳታብስ ቀና ብላ አየችውና መልሳ አቀረቀረች።

 

“ እስቲ በናትሽ ንገሪኝ!ለማወቅ ብቻ! ”

“ ወንድሞቼ ጋር እንደምሄድ ነግሬው ነዋ የምመጣው!” በለቅሶ ዜማ።

“ ስታመሺስ? ”

“ እሱ እንኳ ቀላል ነው።” አለች አስናቀ ልቡ የለሰለሰ መስሏት ምስጢር ባለመደበቋ ይበልጥ አሸነፍኩ ብላ “ኦቨር ታይም ስሰራ ቆይቼ ነው እለዋለሁ”

“ እውነትም ኦቨር ታይም! ” አለ።የብሽቀት ፈገግታ ፊቱ ላይ ነበረበት።

“ ባለፈው ጊዜስ ያን ያህል ቀን የጠፋሽብኝ ለምን ነበረ? ”

 

ለማስታወስ ሞከረች።እንዳልረሳችው ግን አውቆባታል።

 

“ እ..ያኔማ እሱ ታሞ ስለነበር እሱ እያጣጣረ የኔ መዝናናት በጣም ስለቀፈፈኝ ነው አስናቅዬ።ግን ምን ያህል እንደተሰቃየሁ እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው! ”

 

ትዳር የያዘችው ለምንም ይሁን ለምን ለባለቤቷ ታማኝ መሆን እንደነበረባት አስናቀ በሙሉ ልቡ ያምናል።አልሆነችለትም።ባለቤቷ ታሞ ደግሞ እሷ ከምትወደው ሌላ ሰው ጋር መዝናናት ህሊናዋን ይከብደዋል።እንቆቅልሽ!

 

አንድ ጊዜ ዘውዱ “ አዜብ እንቆቅልሽ ነች።” ያለው ትዝ አለው “ አውቄያታለሁ? አላወቅኳትም?እርግጠኛ አይደለሁም።ፊቷ፣ንግግሯ፣ሳቋ ሁሉ የዋህና እውነተኛ ነው።ሰዎችን የመቅረብና የማቅረብ ችሎታዋም ድንቅ መሰለኝ።በጣም ጠልቆ ያላያት ሰው በአታላይነቷ አያምንም።ባሏን ማሞኘቷም አያስደንቅም።”

 

እና አዜብ ባለቤቷ ታሞ አዛኝቱን ሚስት ሆና ስታስታምመው ወለል ብሎ ታየው።

 

“ እሺ አዜብ የነገርሺኝን ሁሉ አምኜሻለሁ።” ዋሸ  “ ግን በትዳር ላይ ከሌላ ጋር መሄድ ነውር ነውና እስካሁን የተዋዋልነው ይበቃናል።እኔም ብሆን ከአሁን ወዲያ በሌላ ሰው እንደምትታቀፊ እያወቅኩ እንደቀድሞው ተረጋግቼ ልወድሽ አልችልም።ወንድምና እህት እንሁን! ” አላት ከልቡ።

 

እንባዋ እንደገና እንደ በጋ ዝናብ ዱብ ዱብ ይል ጀመር።

 

“ አስናቀ! አስናቀ! ባሌን ያገባሁት ለትዳር ነው።አንተን የያዝኩት ግን ለፍቅር ነው እመነኝ! እስቲ አስጨርሰኝ! እንደፈለግክ እሆንልሃለሁ!” እያለች ትከሻውን፣ደረቱን፣አሻሸችው።ከከናፈሩ ጀምራ ግንባሩን፣ጆሮዎቹን፣ጉንጮቹን በሞቃት ከንፈሮቿ አዳረሰቻቸው።በትኩስ እንባዋ አጠበቻቸው።

 

አስናቀ የመንፈሱ ጥንካሬ ደካማ ስጋውን አለመደቋቆሱ አበሳጨው።

 

***

…ነቃች።ፊቷን ወደሱ አዞረችና አፀፋውን መለሰችለት።እንዲህ እንደሆኑ ቆዩ…ቆዩና ሌሊቱ በንጋት ተተካ።አስናቀ የመጨረሻ ውሳኔውን በጥሞናና በፅናት ከገለጸላት በኋላ ከወገቧ በላይ ራቁቷን እንደሆነች እንባ ባቆረዘዙ አይኖቿ ትኩር ብላ ተመለከተችው።የመንፈስ ቅለት ቢሰማውም ሆዱን ባር ባር ማለቱ አልቀረም።ውሳኔው ምን ያህል እንደሚፀናም ርግጠኛ አልነበረም።መስኮቱን ከፈተና የተክለ-ሃይማኖትን አደባባይ ዙሪያ ተመለከተ።ቡትቷሞቹ በረንዳ አዳሪዎች ከሞላ ጎደል ከመኝታቸው ተነስተዋል።ፀሀይም ደማቅ ጨረሮቿን መፈንጠቅ ጀምራለች…

 

ሐምሌ 1975


Print Friendly