ንጉስ ሆይ ሞቅ ብለዎት እንዳይሆን: ALEX Abrehame – በነገራችን ላይ

መፀሃፍ ቅዱስ አንብብ እያለች ንዝንዝ ችክችክ የምታደርገኝ ልጅ ነበረች(ዝንሻ የት ይሆን ያለሽው? እኔ እንኳን ‹‹በዚች አሳባ ልጠብሽኝ›› መስሎኝ ነበር ) ፡፡ ፍሬሽ እያለን የጀመረች ስትነዘንዘኝ ስትነዘንዘኝ…. እሽ እያልኳት ቆይቸ አምስተኛ አመት ላይ መፀሃፍ ቅዱስ የሚባለውን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ አነበብኩ !! እንደፊክሽን ነበር ከመጀመሪያው የጀመርኩት…ከባድና ጥቁር ሽፋኑን ገለጥ ሳደርግ ሌላ ባዶ ጠንካራ ገፅ ..ያንንም ገለጥ….

መፀሃፍ ቅዱስ
የብሉይና የሓዲስ ኪዳን መፃህፍት
በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ታተመ…..
ከዛ ማውጫ…..ማውጫው ግራ አጋባኝ ….ኦሪት ዘ ፍጥረት “ኦሪትም” …. ‹ዘ› ም … ፍጥረትም ……ምን እንደሆነ አላውቅም
ኦሪት ዘ ፀአት …የባሰው መጣ
ኦሪት ዘሌዋዊያን …….ዝም ብየ ማውጫውን አየሁ አየሁና ‹‹ትንቢተ ዳንኤል›› የሚል ሳይ በቃ ይሄን ላንብብ አልኩ….ምክንያቴ ትንሽ ያስቃል ፡፡ ዘጠነኛ ክፍል አብረን የተማርን ቆንጆ ልጅ ስሟ ቃል በቃል ‹‹ትንቢተ ዳንኤል›› የሆነ ነበረች እና የስሟን ሚስጥር ማወቅ አጓጓኝ ….

ዳንኤልን ሳነብ እሷን እረሳኋትና ታሪኩን በጣም ወደድኩት ደጋግሜ ደጋግሜ አነበብኩት ! የገረመኝ ታዲያ 5 ዓመት ሙሉ እኔን አንብብ እያለች ስትነዘንዘኝ የነበረችውን ልጅ ስለትንቢተ ዳንኤል ስጠይቃት ‹‹እኔ እንኳን አላነበብኩትም አብርሽ›› አለችኝ!! ገርሞኝ ልሞት!! (ዝንሽ እስካሁን መቸስ አንብበሻዋል! ለነገሩ እንደኔ ከላይ ከላይ ማለቴ ሳይሆን አንብቦ ለመለወጥ ወላ ለነፍስ ጉዳይ)

ለማንኛውም ዛሬ ትንቢተ ዳንኤል ላይ የመሰጠኝን ታሪክ ላውራችሁ ታውቁታላችሁ ግን በቃ ላውራችሁ ምናለበት ብትሰሙኝ….
ሲጀምር ያለውን እንተወውና የሆነ ናቡከደነፆር የሚባል አምባ ገነን ንጉስ አለ(ከአምባ ገነን ስለጀመረኩ ይቅርታ) …እኔ እንኳን ተመችቶኛል ንጉሱ

….ነገረ ስራው ያስቃል ህልም አየና ህልም ፈች አስጠራ፡፡ ከዛ ህልም ፈችወቹ ‹ይበሉ ንጉስ ሆይ ህልመዎትን ይንገሩንና ብትንትን ብጥርጥር አድርገን እንፍታው ›› ምናምን አሉ፡፡ በሆዳቸው ‹‹ንጉስ ሆይ ህልመወት ሲሳይ ነው›› ሊሉ ተዘጋጅተው ንጉሱ ምኑ ጅል….

‹‹ በሉ እናንት የአገሬ ምርጥ አስማተኞች… አዋቂወች…ሙህራንና ፖለከኞች ….. መጀመሪያ ምን ህልም እንዳየሁ ንገሩኝ እግረ መንገዳችሁን ፍቱት ››ብሎ ቤተ መንግስቱን ቀውጢ አደረገው!! ምድረ ጠቢብ ኢቲቪ ላይ ማትሪክ ሊኮርጅ እንደሚቅበዘበዘው የማስታወቂያው ልጅ ጭንቀት ዋጣቸው አይናቸው ቃበዘ!! ‹‹ያየሁትን ህልም እረስቸዋለሁ ጠቢብ ሁሉ ጠንቋይ ሁሉ ወላ ካድሬ ሁሉ የሰው ህልም እየሰሙ ማዳነቅ ብቻ አይደለም ህልም ከነፍችው ውለዱ›› አላቸዋ ከየት ያምጡ !

የሰው ህልም ላይ ትንታኔ ሲሰጡ የሰው ህልም ‹ሸር› ‹ ኮሜንት› ‹ታግ› ሲያደርጉ የኖሩ ሁሉ ህልም ከየት ያምጡ !ሁሉም አቢወታዊ እርምጃ ተወሰደባቸው(ሂሂ)……. እና ይሄ ንጉስ ሌላ ቀን የራሱን ሃውልት ከወርቅ አሰራና የሆነ ሜዳ ላይ አስተክሎ ‹‹… ህዝቤ ሁይ ውጣ የሃውልቴ ምረቃ ነው ለሃውልቴ ስገድ ››ብሎ አዘዘ!! ካልሰገድክ እሳት ውስጥ ነው የምወረውርህ አላቸው እንደበቆሎ !!

ተቆጠረ 1…2…3….አዳሜ በግንባሩ ተደፋ! ሃውልቱን አክብሮ ሳይሆን እሳቷን እያሰበ …ንጉስ የለኮሳትን እሳት የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ወላ ማንም አያጠፋትም…. እና ህዝቡ በግንባሩ ሲደፋ ሶስት ጥጋበኛ ጎረምሶች እንደአገር ጎብኝ ዘና ብለው ቁመው ታዩ….‹‹እዛጋ! እንጨት ውጣችኋል አትሰግዱም›› ብሎ ባለ እምቢልታ አንዴ አንባረቀባቸው! ወይ ፍንክች! ‹‹እንጨትማ የዋጠው የንጉስህ ሃውልት ነው ጎንበስ አይል ቀና ድንጋይ! እዚህ ተገትሮ በፍቅር ሳይሆን በትዛዝና ማስፈራሪያ ህዝብ እያሰገደ ያነጅባል› ብለው እያሰቡ ….

ለንጉሱ ተነገረው ‹‹ንጉስ ሆይ ኧረ የሆኑ ፍንዳታወች ገጥመውናል ለአንተ ምስል አንሰግድም ብለው እንደጅብራ ተገትረዋል››
‹‹ጆሯቸውን ይዛችሁ እያዳፋችሁ አምጡልኝ እከከከከከከከከ››
ሶስቱ መልከ መልካም ወጣቶች ንጉሱ ፊት ቀረቡ…
‹‹እናንተ ናችሁ ከወርቅ ላሰራሁት ሃውልቴ አንሰግድም ያላችሁት››
‹‹አዎ ንጉስ ሆይ አሉ በትህትና….›› ንጉሱ ለመልሳቸው ስም አወጣለት ‹‹ብልግ ያለ ትህትና›› ሲል

‹‹ለምን ቢባል?›› ንጉስ ጠየቀ
‹‹ ሃውልቱ አልታየንም ›› ከሶስቱ ዳንኤል የሚባለው መለሰ ይሄ ዳንኤል ካሁን በፊት የንጉሱን ህልም ከነፍችው የተናገረ ነብይ ነው ‹የራሱ ህልም ያለው ሰው ለማንም ቅዠት ሲሰግድ አይኖርም› ዳንኤል ህልም አለው!!
‹‹አልታየንም?….ስልሳ ክንድ ቁመት ስድስት ክንድ ወርድ ያለው ሃውልት … ያውም የወርቅ ሃውልት አልታያችሁም ?››
‹‹ አዎ ንጉስ ሆይ ሃውልትህ አልታየንም›› ኮራ ብለው መለሱ
‹‹እውር ናችሁ…››
‹‹አይደለንም! ግን ከአንተ ሚጢጢ ሃውልት ፊት ሌላ ግዙፍ ህያው ምስል ቁሞ ስለነበር ጋረደን››
‹‹ማነው እሱ ከእኔ የገዘፈ ….››ንጉሱ ፀጉሩን ነጨ
‹‹እርሱ መለኪያ የሌለው ሰማይ ብርኩማው ምድር <የሊስትሮ ሳጥኑ> እግሩን የሚያሳርፍባት…. እግዚአብሄር ነው እኛንም አንተንም የፈጠረ››

ንጉሱ እነዚህን ሰወች ለአይኑ ጠላቸው አንገሸገሹት አንገበገቡት ‹‹ውሰዱና እሳት ውስጥ አስገቡልኝ ማን እንደሚያድንህ አየያለሁ እያንዳንድህ›› እንደአሪፍ ቲያትር ንጉሱ ፊት ለፊት ጉዳቸውን ሊያይ በዚያውም ደፋሮቹ አመድ ሲሆኑ እያየ ዘና ሊል …. ሰባት እጥፍ በነደደ እሳት ውስጥ ህዝብ እያያቸው ሶስቱም ተወረወሩ፡፡

አንዳንድ የዘመኑ ነዋሪወችም ‹መንግስት በሶስቱ ሰወች ላይ የወሰደው እርምጃ ተገቢ ነው እንደውም የመንግስት ትእግስት በዝቷል› ሲሉ ተሰሙ!! አለመስገዳቸው አስወረወራቸው ያለ አልነበረም ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ (ፀረሰላም በጥባጭ አዋኪ የህዝብንና የመንግስትን ሰላም ያደፈረሱ የወርቅ ሃውልቱን በሃይል ለመናድ የሞከሩ ክሳቸው ነበር) የእሳቱ ወላፈን ወርዋሪወቹን በላና እርሃቡን አስታገሰ….

አዚች ላይ ነው አሪፍ ነገር የተፈጠረው እሳቱ ዳኛ እንዳዘዘው የፍርድ ቤት ፖሊስ የእስረኞቹን ገመድ ፈታና ሶስቱም በእሳቱ ውሰጥ ሰበር ሰካ እያሉ ሲመላለሱ ታዩ ኧረ አራት ናቸው …. !!

ደግሞ ለተንኮሉ መጀመሪያ የታየው ለንጉሱ ነው….ሪፖርት ተሳስቶ ነው ምናምን እንዳይባል!! ‹‹እንዴ ቆይ ስንት ነበሩ እነዚህ ልጆች ›› ጣቱን እየቆጠረ ስማቸውን እየጠራ ቢደመር ሶስት! ቢያባዛ 3 ! ቢቀነስ 3 !ወይስ እንደፈንዲሻ እሳት ውስጥ ሲገቡ ይበዛሉ… እና አራተኛው ሰው ማነው? ማነው ይሄ ድንኳን ሰባሪ (ማለት እሳት ሰባሪ)….አአአ ግርማ ሞገሱ ድንኳን ሰባሪ አይመስልመ…..ምናምን አሉ….

ንጉሱ ባነነ ሂሳቡን አቁሞ በ ‹ፒስ› ወደሳቱ ጠጋ አለ እና ጉሮሮውን ጠራርጎ በዜማ ‹‹ ገባኝ አሁን ገና ገባኝ አሁን ገና …›› ሃሃሃሃሃ ሰናፊላ (ምንድነው ግን ሰናፊላ) ብቻ ሰናፊላቸው አልተቃጠለም……ሲወጡ ኮራ ብለው ሲወጡ ….ስልጣን በስልጣን አደረጋቸው ….በስልጣናቸው አልባለጉም በእሳት የተገኘ ስልጣን ነው ብለው ሙጭጭ አላሉም ……ይለናል መፀሃፉ ሳናውቅ በስህተት እያወቅን በድፍረት ለጨማመርነውና ለቀናነስነው ይቅር ይበለን!! አሜን!!


Print Friendly