ወያኔ «ላሊበላ ትግራይ ውስጥ የሚገኝ ውቅር አብያተ ክርስቲያን» መሆኑን ለአለም አስታወቀ!

By Achamyeleh Tamiru

ወያኔ «ላሊበላ ትግራይ ውስጥ የሚገኝ ውቅር አብያተ ክርስቲያን» መሆኑን ለአለም አስታወቀ!

በሳለፍነው ጥር ወር 2008 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሳምንት አካባቢ ወያኔ በኢትዮጵያ ለረጂም አመታት ሲሰራበት የቆየውን የቱሪዝም አርማ ለመለወጥ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን በህወሀቱ የቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ በሰለሞን ታደሰ በኩል በዜና እወጃው ነግሮን ነበር።

ብዙ ሰው እንደሚያውቀው የኢትዮጵያ ቱሪዝም መስሪያ ቤት «የኢትዮጵያ የቱሪዝም አባት» የሚባሉት አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሸን ሚንስትር በነበሩበት በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ «የአስራ ሶስት ወር ጸጋ» በሚል መርህ የአገራችንን ቱሪዝም ለአለም ለማስተዋውቅ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል። በዚህም መሰረት «የአስራ ሶስት ወር ጸጋ» ባለቤቱ አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ የሚመሩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቱሪዝም ኮሚሽን ድንቅ የሆኑ ፎቶዎችን አንስቶ በየኢምባሲዎች፣ በአየር መንገዳችን መጽሄቶች፣ በቴምብርና በልዩ ልዩ ህትመቶች ያወጣ ነበር።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን «የአስራ ሶስት ወር ጸጋ» በሚል ርዕስ ካሳተማቸው በርካታ ፖስተሮች መካከል የዝነኛዋ «ውቢት ኢትዮጵያ» አስደናቂ ተፈጥሮአዊ ውበትና ግርማ ሞገስ የታየበት ተደዳጅ ፖስተር ሁሌም ከማይረሱት የኢትዮጵያ ምልክቶች መካከል አንዱ ነው።

«ውቢት ኢትዮጵያ» የአራት ልጆች እናት የነበረችው የወለጋዋ አልማዝ አመንሲሳ ናት። አልማዝ አመንሲሳ ወለጋ ተወልዳ አድጋ ከልጆቿና ለቱሪዝም ኮሚሽን ተቀጥሮ ይሰራ ከነበረው ባለቤቷ ጋር አዲስ አበባ ትኖር ነበር። አልማዝ ሞዴል ወይ የፊልም ተዋናይት አልነበረችም። በቱሪዝም ኮሚሽን ፎቶ የመነሳት እድል አግኝታ ግን <<ውቢት ኢትዮጵያ>> ሆና አገራችንን ለአለም አስተዋውቃለች። አልማዝ አመንሲሳ በ2000 ዓ. ም. ለህክምና ወደ አሜሪካ ብትመጣም ህመሟ ጸንቶ ህዳር ወር 2001 ዓ.ም. ከዚህ አለም በሞት ተለይታለች።

ኢትዮጵያን በቱሪዝም የአፍሪካ ቁንጮ የማድረግ እቅድ በነበራቸው በቱሪዝም አባታችን በአቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ ቦታ የተቀመጠው የህወሀቱ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን ታደሰ በአለም የታወቅንበትን ኢትዮጵያዊ መልክ ያለው የቱሪዝም አርማ ፍቆ የጠላት አገር የተረከበው ወያኔ የሰጠውን ትዕዛዝ በመቀበል «ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም እምቅ ሀብት አሟልቶ የማያሳይ» በሚል ሰበብ ረብጣ ዶላር እየተከፈለበት በአለም ዙሪያ እየሳየ ባለው ከታች በታተመው አዲሱ «የኢትዮጵያ» ቱሪዝም ማስታወቂያ «ላሊበላ ትግራይ የሚገኝ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ነው» ይለናል! በቱሪዝም ማስታወቂያ ስም ወያኔ የትግራይን ማስተር ፕላን ለአለም እየነገረ ነው።

ወያኔዎች በአንደኛ ደረጃ ማስተማሪያ መጽሀፍ ውስጥ «ራስ ዳሸን በትግራይ የሚገኝ ተራራ» እንደሆነ ለትግራይ ልጆች እያስተማሩ ነው። ባገር ቤት ልጆቻቸውን በትግርኛ፤ በውጭ ደግሞ ለቀሪው አለም በእንግሊዝኛ «የትግራይ ነው ወይንም መሆን አለበት» ብለው የሚያስቡትን ሁሉ በኛ ገንዘብ ማስታወቂያ እየሰሩ፤ እኛ ግን ዘረፋቸውን፣ ግፍና በደላቸውን በተቃወምን «ዘረኛ!» ይሉናል። ግብኑ ብቻ የሚንቀሳቀሰው የኛ ሰውም እነሱን እየተከተለ አብሯቸው «አዎ ልክ ናችሁ ዘረኞች ናቸው» ይላል። ባጭሩ እነሱ «የትግራይ ነው ወይንም መሆን አለበት» በማለት ሊወስዱት ያሰቡትን ለታሪክ ጸሀፊዎች፣ ለጎብኝዎችና በአጠቃላይ ለአለም ማህበረሰብ በማስተማር ረገድ የዚያ የተረገመ ትውልድ አካል የሆነው የኛው ሰውም ከጎናቸው ነው።

ይህ ታይቶት ይሆን ተወዳጁ የባህል ዘፈኝ ቻላቸው አሸናፊ በሚያዝገመግመው ድምጹ እንዲህ ያንጎራጎረው፤

ጠበቃሽ ማን ይሆን፣
እማሽስ ማን ይሆን፣
ዋስሽስ ማን ይሆን፣
የነበረሽ ሁሉ እንዳልነበር ሲሆን…
***
እትብቴ ከወድያ መቃብሬ ወዲህ፣
በተወለድኩባት አልኖርኩም ከ’ንግዲህ፤
***
ሲጠፋ እየታየው እልፍኝ አዳራሹ፣
አይጨነቅም ወይ ለነገው ወራሹ፤
***
ጠበቃሽ ማን ይሆን፣
እማኝሽ ማን ይሆን፣
ዋስሽስ ማን ይሆን፣
የነበረሽ ሁሉ እንዳልነበር ሲሆን…


Print Friendly