ወይ ህይወት…

06 March 2014

ወይ ህይወት፡
ድሮ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሁኘ ያነበብኳት ነገር ሁሌም ትገርመኛለች፡፡
በትምህርታቸው ጎበዝ የሆኑ፣ ብሩህ አእምሮ ያላቸው Class A ተማሪዎች በብዛት የተፈጥሮ ሳይንስ (Natural sciences) መርጠው ትምህርታቸውን ይቀጥሉና ዩኒቨርሲቲም ገብተው ዶክተሮች፣ኢንጂነሮች፣ የሳይንስ ተማራማሪዎች፣ ቴክኖሎጂስቶች ወ.ዘ.ተ ይሆኑና የዐለማችን የሰራተኞችን መደብ ይፈጥራሉ፣ ለዐለምም ጠቃሚ ግኝቶች ያገኛሉ፣ ዐለምንም ያገለግላሉ፡፡ ጥቂቶችም በማሕበራዊ ሳይንስ ዘርፉ የሕግ ባለሞያ በመሆን የለምን ሕግን ያስከብራሉ፣ ፍትሕን ይሰጣሉ፣ ያሳጣሉ፡፡(እዚጋ የማሕበረሰብ ሳይንስ የሚመርጡ በዛም ዘርፍ የሚቀጥሉና ታላላቅ አስተዋፅኦ የነበራቸውም በርካታ ጎበዞችም አይተናልና ይህ እንዲታወቅ ይሁን፡፡)

ከነሱ ቀጥለው ያሉት መካከለኛ ተማሪዎች Class B ተማሪዎች በብዛት የማሕበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ይቀላቀላሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ ማናጀሮች፣ ኢኮኖሚስቶች ወ.ዘ.ተ በመሆን ቀዳሚዎቹን ጎበዞቹን Class Aዎችን ያስተዳድራሉ፣ ያሽከረክራሉ፣ ያዛሉ፡፡

Class Cዎች ደግሞ አሉ፡፡ እነዚህ በትምህርትም በአስተሳስብ አድማስም ነፈዝ የሚባሉ ናቸው፡፡ ብትምህርትም መግፋት አልሆን ስለሚላቸው ከ8ም ከ10ም ወድቀው ያቋርጡና በአቋራጭ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚሆኑበትን ማንኛውም መንገድ ይዘይዳሉ፡፡ እናም ነጋዴዎች ወይም ፖለቲከኞች ይሆናሉ፡፡ ወይም ነፍጥ አንግበው ጫካ ይገባሉ፡፡ እነዚሁ በአቋራጭም የዐለማችንን ሀብት፣ ጉልበትና ጭንቅላቶችን ያዛሉ፣ ይበዘብዛሉ፡፡ ሁለቱንም Class A ና Class Bዎችን ያዛሉ፣ ይገዛሉ፣ ያሽከረክራሉ፡፡ ዐለምም በነሱ ቁጥጥር ስር ናት፡፡

እኛ ሀገር ያሉት በሁሉም ዘርፍና የስልጣን ተዋረድ ያሉት አብዛኛዎቹ ሙጃዎች፣ ደም መጣጮችስ ምን እንበላቸው? በተለይም እዚሁ እኔ ካለሁበት ክልል የተለያዩ ሹማምንቶችን ሳይ ሁሌ እንደተገረምኩ ነው፡፡ ህሊና-ቢስነት፣ ጭካኔ፣ ዋሾነት፣ ስግብግብነት መለያቸው ሁኖ፤ ወይ ከትምህርቱ፣ ወይ ከንግዱ፣ ወይ ከፖለቲካው ወ.ዘ.ተ በአንዱም ጥሩ ሳይሆኑ ፤ ምንም ይህ የሚባል ደህና ነገር ሳይኖራቸው ጥሩው ኢትዮጵያዊ በተወላቸው ቀዳዳ ተጠቅመው ሁሉንም ነገር በቁጥጥራቸው ሰተት ብሎ ገባና በቃ ሁላችንም የእግራቸው መርገጫ አደረጉን፡፡ እነዚህ በሶስተኛው Class C ላይ እንኳ ለማካተት የማይበቁ ናቸው፡፡


Print Friendly