የትኛው ነው ታማኝ fanabc.com or ertagov.com

የትኛው ነው ታማኝ

ፋና-ኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብጽ በግድቡ ዙሪያ በካርቱም ያደረጉት ውይይት ያለውጤት ተጠናቀቀ

ERTAgov.com-ሶስቱ ሀገራት በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ተቀራርበው ለመስራት ተስማሙ

fanabc.com

ኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብጽ በግድቡ ዙሪያ በካርቱም ያደረጉት ውይይት ያለውጤት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 26 ፣ 2006 (ኤፍ ቢ ሲ)  አለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስመልክቶ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ባስቀመጣቸው ቀጣይ የትኩረት ነጥቦች ላይ በሱዳን መዲና ካርቱም ለአንድ ቀን ሲካሄድ የነበረው የሶስትዮሽ ውይይት ያለ ውጤት ተጠናቋል ።

የታችኛው የአባይ ተፋሰስ ሃገራት ግብጽና ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመሩን ተከትሎ ከውሃ መጠንና ከግድብ ደህንነት ጋር አለን ያሉትን ስጋት መነሻ በማድረግ ነበር ።

አለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም ተደርጎ በተነሱት የሁለቱ ሃገራት ስጋቶች ላይ ወራትን የፈጀ ጥናት አካሂዷል ።

ሶስቱም ሃገራት እኩል የተሳተፉበት ይህ ቡድን በስተመጨረሻ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ግድቡ በሁለቱ ሃገራት የተነሱትን ስጋቶች እንደማያስከትል በአጠቃላይም በታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት ላይ ጉልህ የሆነ ተጽእኖ እንደማይኖረው ያረጋገጠ ነው ።

ቡድኑ ይህንን ውጤት ይፋ ከማድረግ ጎን ለጎን ቀጣይ ስራዎች ምን ሊሆኑ ይገባል በሚለው ዙሪያም አስተያየቶችን አስቀምጧል ።

እነዚህም ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት የሚፈጥረው የአካባቢና የህብረተሰብ ተጽእኖ  እንዲሁም የሃይድሮሎጂ ሞዴሊንግ በሂደት ሊታዩ ይገባል የሚሉ ናቸው ።

በእነዚህ የአለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን የመጨረሻ አስተያየቶች ላይ በቀጣይ ሊደረጉ ስለሚገባቸው ክትትሎች ለመምከር  የሶስቱ ሃገራት የውሃ ሚኒስትሮች በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም ተገናኝተዋል ።

የኢፌድሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ  ከስፍራው ሆነው ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እስከ ትላንት ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ የቆየው ስብሰባ በመጨረሻው መግባባት ላይ ሳይደረስ ተጠናቋል ።

በውይይቱ ከሙሉ መግባባት እንዳይደረስ ያደረገው የአለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን በቀጣይ ሊታዩ ይገባል ብሎ ያስቀመጣቸውን ጉዳዮች የሚከታተልን ኮሚቴ በምን መልኩ ማዋቀር ይገባል በሚለው ሃሳብ ላይ ልዩነት በመፈጠሩ ነው ።

ለስምምነቱ አለመደረስ ምክንያት የሆነውም በግብጾች በኩል የቀረበው የተለየ ሃሳብ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነው ።

በዚህም ሳቢያ ሃገራቱ ከቀጣይ መግባባት ላይ ለመድረስ መልሰው ከአንድ ወር በኋላ ካርቱም ላይ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል ።

አቶ አለማየሁ እንዳሉት የሶስትዮሽ ስብሰባው ከዚህ በተጨማሪ በሌሎች ግድቡን የተመለከቱ ጉዳዮችም ተነጋግረዋል ።

በሱዳን በኩል አሁንም ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የማድረግ አቋሟ የቀጠለ ሲሆን ግብጾችንም በግንባታው ላይ መተማመን እንዲያድርባቸው የሚያደርጉ ሃሳቦች በውይይቱ መንጸባረቁንም አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።

 

በአንዱዓለም ሽመልስ

 

ertagov.com

ሶስቱ ሀገራት በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ተቀራርበው ለመስራት ተስማሙ

ሱዳን፣ግብፅና ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ በተቀመጡት የመፍተሄ ሀሳቦች ላይ ተባብሮና ተቀናጅቶ ለመስራት ዳግም ተስማሙ፡፡

ሰኞ ጥቅምት 25/2006 ሶስቱ የታችኛው ናይል ተፋሰስ ሀገራት ሱዳን፣ግብፅና ኢትዮጵያ እየተገነባ ባለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የነበራቸውን ልዩነት ለማጥበብና ተባብሮ ለመስራ የሚያስችላቸውን ምክክር በሚኒስትሮች ደረጃ ማካሄድ ጀምረዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ በታችኛው የተፋሰሱ ሀጋራት በተለይም ግብፅና ሱዳን ላይ ጉዳት ሊያስክትልብን ይችላል፤የውሀ ድርሻችንንም ይቀንስብናል የሚለውን አለመግባባት ለመፍታት በሀገራቱ ስምምነት የተቋቋመው አለም አቀፍ የአጥኚዎች ፓናል ቡድን የመፍትሄ ሀሳብ ማቅረቡም ይታወሳል፡፡

የባለሙያዎቹ ቡድንም የግድቡ ግንባታ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት አሉታዊ ተፅዕኖ እንደማኖረውና ነገር ግን ሀገራቱ ተባብረውና ተማምነው በመስራት ሊፈጠር የሚችለውን ስጋታቸውን መቀነስ እንደሚችሉም አስቀምጧል፡፡

በእነዚህና በሌሎች የባለሙያዎቹ የመፍትሄ ሀሳቦች ትግበራ ላይ ለመወያየት ካርቱም ላይ የተሰባሰቡት ሶስቱ ሀገራት ታድያ ፣ዳግም በግድቡ ግንባታና በመፍትሄ ሀሳቦቹ ቀጣይ ትግበራ ላይ ተባብሮና ተቀናጅቶ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የቻይናው ዜና አገልግሎት ሽንዋ ዘግቧል፡፡

የሱዳኑ የውሃና አሌክትሪክ ሀይል ሚንስትሩ ኦሳማ አብደላህ በውይይታቸው፣ ሀገራቱ በግድቡ ግንባታና ተፋሰሱ የብልፅግና ምንጭ መሆን በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ ለመስራት መነሳሳት ማሳየታቸውን ተናግረዋል፡፡ሱዳንም አለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ላቀረበው ሀሳብ ትግበራ በሙሉ አቅሟ እንደምትተባበር ገልፀዋል፡፡

የግብፁ የውሃ ሀብትና መስኖ ሚንስትር ሙሃመድ አብደልሙጦሊብ በበኩላቸው ሀገራቱ  የጀመሩት ምክክር ለህዝቦቻቸው ልዩ ጥቅም አዲስ ምዕራፍ መክፈትና የተሻሉ ስትራቴጅዎችን መቀየስ በሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብለዋል፡፡በትብብር ሂደቱም ሀገራቱ ተጨባጭ ውጤት ላይ ይደርሳሉ የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የመስኖ ፣ውሃና ኢነርጂ ሚንስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለህዝቦቿና ለቀጠናው ልማት በሚል እየገነባች ያለው ግድብ ለሁሉም ሀገራት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በሂደቱም በቀጠናውና የተፋሰሱ ሀገራት መካከል የጋራ መተማመን እንዲፈጠር ኢትዮጵያ አበክራ ትሰራለች ብለዋል፡፡የግድቡ ግንባታም የአለም አቀፉ የአጥኚዎች ቡድን ያስቀመጠውን የመፍትሄ ሀሳብ መሰረት አድርጎ እንደሚካሄድም ሚንስትሩ ተናግረዋል፡፡

ሶስቱ ሀገራት በስብሰባቸው ማጠቃለያ ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን መግለጫ ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 


Print Friendly

Leave a Reply