የፈረደበት ግንቦት 7፤ የፈረደባት ኤርትራ (ለአቶ ያሬድ ኃ/ማርያም አንዳንድ መልሶች)

Ecad Forum

ተከልሚካኤል አበበ (ቶሮንቶ፤ ካናዳ)

ለአቶ ያሬድ ኃ/ማርያም አንዳንድ መልሶች፤

እንደመግቢያ፤ ያሬድና ጽሁፉ

1-      አቶ ያሬድ ሀይለማሪም (ያሬዶ) ለሰብአዊ መብት መሟገት አመል ሆኖበት (አመሉ፤ አዎንታዊ በሆነ መልኩ ማለቴ ነው)፤ ከጥቂት ቀናት በፊት አንድ ጽሁፍ አውጥቶ ነበር፡፡ ያንን ጽሁፍ ተከትሎ አንዳንድ በብእር ስም ጀርባ የተደበቁ ተቺዎች አበሳጩት መሰለኝ ሌላ ተከታይ ሁለተኛ ጽሁፉም ጽፎዋል፡፡ የኔ አስተያየት በመጀመሪያው ጽሁፍ ላይ ነው፡፡ ከሞላ ጎድል ጽሁፉ፤ ግንቦት ሰባት፤ ለኢትዮጵያ እንታገላለን ብለው ኤርትራ የገቡ ወጣቶች ላይ፤ ከኤርትራ መንግስት ጋር በመተባበር፤ ብዙ ግፍ እየፈጸመ ወይንም እያስፈጸመ ሲሆን፤ መገናኛ ብዙሀን ይሄ ግፍ ሲፈጸም እያዩ ዝም ማለታቸው፤ አግባብ አይደለም የሚል ነው፡፡ የያሬዶ ጽሁፍ ሸጋ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፤ ያሬድ፤ በሰዎች ልቅሶ ተሸንፎ ይሁን በአስተሳሰብ ስህተት፤ በጽሁፉ፤ አያሌ የአቀራረብ፤ የክርክርና የጽንሰ ሀሳብ ስህተቶችን ፈጽሞዋል፡፡ እያንዳንዱን ስህተቶቹን ነቅሶ ለማውጣት ጊዜ አይበቃም፡፡ ስለዚህ ዋና ዋና ያልኩዋቸውን ስህተቶቹን ከዚህ እንደሚከተለው ለማስረዳት እሞክራሁ፡፡

2-     ለማሳሰቢያ ያህል፤ ካልተሳሳትኩ፤ ያሬድን ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ውስጥ ሲሰራ አውቀዋለሁ፡፡ በአገርወዳድነቱና በሀቀኛነቱ ማንም የማይጠይቀው ግሩም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ያሬድን መሞገት የሚፈልግ ሰው ካለ ያለምንም ጥርጣሬ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት በያሬድ ሰብእና ላይ ሳይሆን በጽሁፉ ላይ ነው፡፡ ያሬዶም፤ እንደኔ ቆዳው እስኪደነድን ድረስ፤ አንዳንድ ጠንከር ያሉ ጽሁፎችን ሲጽፍ ዘለፋ የሚተፉትን ከተፋ የሚወዱትን እንዳላየ ቢያልፋቸው እመክራለሁ፡፡ በጽሁፉ ላይ እነሆ አስተያየቴን፡፡

ኦሬንጅና አፕልን የመደባለቅ ያህል

3-     ያሬድ ክርክሩን የጀመረው፤ በሳኡዲአረቢና፤ በሱዳን፤ በየምንና በሌሎች አረብ አገራት ስለሚበደሉ ኢትዮጵዊያን ሲጮሁ የነበሩ መገናኛ ብዙሀን፤ በኤርትራ ስለሚበደሉ ኢትዮዊያንስ ለምን አይጮሁም በማለት ሁለት የማይነጻጸሩ ነገሮችን፤ ብርቱካንና አፕልን በማወዳደር ነው፡፡ በርግጥም ስራ እናገኛለን፤ እንጀራ ይወጣልናል፤ ለራሳችንም ለቤተሰቦቻችንም ያልፍልናል ብለው ወደተጠቀሱት አገሮች የሄዱ ሰዎች፤ በሰላም አገር፤ መንግስት እና ህግ ባለበት፤ አግባብ ያለሆነ ግፍ ሲደርስባቸው፤ ሲሆን ሲሆን ፓስፖርት የሰጣቸው መንግስት ሊጠብቃቸው ይገባ ነበር፡፡ ያ አልሆነም፤ ስለዚህም ሁላችንም የመጮህ ግዴታችን ተወጣን፡፡ ጮህን፡፡

4-     ወደኤርትራ የሄዱት ወጣቶችም ወደኤርትራ የሄዱት ራሳቸውንም አገራቸውንም ነጻ ለማውጣት ቢሆንም፤ ማንም የትጥቅ ትግልን ሀሁ የሚያውቅ ሰው እንደሚረዳው፤ በድብቅ፤ በስውር፤ ሲሆን ሲሆን ለመግደል፤ ካልሆነም ለመሞት የሄዱ ሰዎች፤ ወደሪያድና ወደሰንአ እንደሄዱ የኢኮኖሚ ስደተኞች የመብት ጥበቃ ይደረግልናል ብለው ካሰቡ፤ ይሄ የሽምቅ ውጊያ ሳይሆን የሽምቅ ቅንጦት ነው፡፡ ሁለቱ የሳኡዲና የኤርትራ ክስተቶች የተከሰቱት ፈጽሞ በተለያዩና በማይመሳሰሉ አግባቦች ነው፡፡ ሁለቱ ጉዞዎች ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል አይነት ነገር ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁለቱን ክስተቶች መደባለቅ በአቶ ያሬድ በኩል የአቀራረብም የአስተሳሰብም ስህተት ነው፡፡

5-     የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞዋል አልተፈጸመም ወደሚለው ክርከር ሳንገባ፤ ከኤርትራ የተመለሱት ልጆች ደረሰብን ያሉት በደል ቢደርስባቸውም እንኩዋን፤ እነሱም ድረሱልን የማለት እኛም ወገኖቻችን አለቁ የማለት የሞራልም የህግም መሰረት የለንም፡፡ የመረጡት የትግል ስልት መሞትን ወይም መግደለን ወይም እዚያው ተሙዋግቶና ተፋልሞ ችግር መፍታትን ነው እንደ ምርጥ ስልት አድርጎ የሚወስደው፡፡ ምናልባት ችግሩ ከከፋና ጣልቃ መግባት ካስፈለገ፤ ያንን ማድረግ የሚችለው ከኤርትራ ጋር ውል ያለው ፖለቲካዊ ግዴታ ያለበት ቡድን ሲሆን፤ ያለው አማራጭ የኤርትራን መንግስት መለማመጥ ነው እንጂ፤ ለሳውዲ ስደተኞች እንደተጮከው ለመጮህ አይቻልም፡፡ ያ አይነቱ አካሄድ ችግሩን ያብሰዋል፡፡ በእስረኞቹም በታጋዮቹም በትግሉም ላይ ማነቆውን ያጠብቀዋል፡፡

የሰላም ሰዓት ሕግን ከጦርነት ህግ መለየት

6-     እንደሚመስለኝ ያሬዶ በጽሁፉ ላይ አንድ መሰረታዊ የጽንሰ ሀሳብ ስህተት ፈጽሞዋል፡፡ ሰብአዊ መብት ሲቪሉ ማህበረሰብ ወይንም ግለሰቦች በሰላም ወቅት ከመንግስታቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚዳኝበት የመብት መጠበቂያ ህግ ወይንም መሳሪያ ነው፡፡ ጦርነት ወይንም የትጥቅ ትግል ውስጥ ስንሆን ግን ነገሮች ይለዋወጣሉ፡፡ በጦርነት ውስት ሰብአዊ መብት የለም ባይባልም፤ የሲቪል አስተዳደሩን ወይንም የሰላም ወቅቱን አይነት ሰብአዊ መብቶችን ጥበቃ መመኘት በትንሹ የዋህነት በጣም ጀበዛ ደግሞ ጅልነት ነው፡፡ የጦርነት ሰዓት የሚገለገልበት ራሱን የቻለ ሰፊ አለማቀፍ ሕግ እንዳለ ያሬዶ አያጣውም፡፡ በዚህ ረገድ የሄግንና የጄኒቫን ስምመነቶችና በዚ ዙሪያ የተጻፊ ትናቶችን ማንበብ ይጠቅማል፡፡

7-     እንኩዋንስ በጦርነት ሰዓት፤ በሰላም ሰኣትም፤ እንኩዋንስ ገና ከሽምቅ ዘመን መንፈስ በቅጡ ባልተቆራረጠችው ኤርትራ፤ በሰለጠኑት አገራት እንኩዋን፤ ወታደር፤ ወይንም ጦር ሰራዊት፤ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፤ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት፤ ስህተቶች እንዲታረሙ የማመጽ፤ የመደራጅትና የመቃወም የሚባሉ መብቶች አይታሰቡም፡፡ ወታደሮች ያለቆቻቸውን ትእዛዝ ያለምንም ማመንታት ይፈጽማሉ ያስፈጽማሉ፡፡ ከዚያ ካፈነገጡ፤ ይቀጣሉ፡፡ ወደሲቪል ፍርድቤትም አይቀርቡም፡፡ በወታደራዊ ፍርድቤት እስከሞት የሚያደርስ እርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ወታደራዊና ሌሎች ምስጢሮችን ለዊኪሊክስ አሳልፎ በመስጠቱ ምክንያት 35 አመት የተፈረደበትን አሜሪካዊውን ብራድሊይ ማኒንግን ያስታውሱዋል፡፡

8-     ስለዚህ በግንቦት ሰባትም ይሁን በኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያዊን ተዋጊዎች ወይንም ሸማቂዎች ላይ የፈጸሙት ግፍና በደል ካለ መዳኘት ያለባቸው፤ ሰብአዊ መብት በሚባል የሰላም ሰዓት፤ የቅንጦት (ጫካ ውስጥ ማለቴ ነው) ድንጋጌ ወይንም መመዘኛ ሳይሆን፤ በራሱ በወታደራዊ፤ ለዚውም በሽምቅ ተዋጊዎች የዳኝነት ስልትና ዲሲፒሊን ነው፡፡ ያሬዶ በጽሁፉ ውስጥ የወታደርንና የሲቪሊን አስተዳደር በመደበላለቅ ከፍተኛ የጽንሰሀሳብ ስህተት ፈጽሞዋል የምለው ለዚህ ነው፡፡

የራሳቻው የሻእቢያና የሕወሀት የድል ጉዞ ምን ያስተምራል

9-     በዚያ መልኩ እንጉዋዝ እንደማለት እንዳታይብኝ እንጂ፡ ራሱን ሻእቢያን ለድል ያበቃውን የ30 አመታት ጉዞ ብንመለከት፤ ወይንም ሕወሀትንም ለድል ያበቃውን የ17 አመታት ፈታኝ ታሪክ ብንዳስስ፤ ያፈነገጡና ያስቸገሩትን መረሸን፤ ማስወገድ የትግሉ ተፈጥሮ የሚጠይቀው በውጤት የተፈተነ ፍቱን መንገድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ፤ ኢህአፓም ደርግም ጎበዝ ናቸው፡፡ ያፈነገጠን፤ የወላወለን፤ የከዳን ይረሽናሉ፡፡ በትጥቅ ትግል ውስጥ፤ የሰብአዊ መብቶች፤ ዴሞክራሲዊ ውይይት፤ በፍርድቤት መዳኘት፤ ሀሳብን የመግለጽ መብት ምናምን የሚባሉ ሀረጎች መታሰብ የለባቸውም፡፡ ስለዚህ አቶ ያሬድ እነዚህን የሰላምና የቅንጦት ሰኣት አስተሳሰቦች አምጥቶ የግንቦት ሰባትን ወይንም የኤርትራን መንግስት ለመውቀስና መገናኛ ብዙሀንም ግፍ ለሚደርስባቸው ሰዎች እንዲደርሱላቸው ይነሱ ማለቱ ስህተት ነው፡፡

10-    ከዚያ መለስ፤ የአንድ ሁለቱን ልጆች ቃለምልልስ እንዳደመጥኩት ከሆነ፤ በልጆቹ ላይ የደረሰውን ነገር ለሚሰማ የእናት/የወላጅ አንጀት ላለው ሲቪል ሰው፤ በርግጥም እንደሰው በልጆቹ ላይ በደረሰው ክስተት ሊያዝን ሊበሳጭ ይችላል፡፡ እንዳጋጠሚ ሆኖ እኔ ልጆቹ ደረሰብን ባሉት ነገር ብዙም አላዘንኩም፡፡ እንደውም ልጆቹ በሰላም ከኤርትራ ከወጡ በሁዋላ ሲሆን ሲሆን ኤርትራን ማመስገን፤ እንበለዚያም አፋቸውን መዝጋት ሲጠበቅባቸው፤ በሬድዮ ላይ ያንን ሁሉ ምስጢር ማውጣታቸው ትክክል አይደለም፡፡ በርግጥም ግንቦት ሰባት ደካማ መሆኑ እንጂ ምስጢር ማውጣትም ይሁን ግንባር ጥሎ መሄድ በሞት የሚያስቀጣ ወታደራዊ እርምጃም ሊያስወስድ ይችላል፡፡ ምክንያም፤ ነገሩን ግንባር ላይ እንደተፈጠረ ክስተት አድርገን ብንወስደው፤ እነዚህ ሰዎች ጥለው በሄዱት ቦታ ጠላት ገብቶ የወገን ጦርን ድባቅ ሊመታ ይችላልና፡፡ ግንባር ሸሽቶ መሄድ ነውርም፤ ትልቅ ክህደትም ነው፡፡

አጥንት አሸንፎን፤ አጽም ዘርሮን

11-     እነዚህ ልጆች ጥያቄ አንስተው መቀጣታቸው፤ ለኤርትራ መንግስትም መሰጠታቸው ከትጥቅ ትግል ባህርይ አንጻር አስገራሚ አይደለም፡፡ እነዚህ ልጆች እኮ የሰላም አስከባሪ ሀይል ሆነው አይደለም ወደኤርትራ የሄዱት፡፡ ቢረሸኑስ ኖሮ፡፡ ምን ያስገርም ነበር፡፡ በረሀብ መሰቃየታቸውም ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ያለፉበት መንገድ ነው፡፡ እነዚህ ልጆች በጣም ህጻነት ካልነበሩ በስተቀር፤ በረሀብና በችጋር የተጎሳቆለ፤ አጥንትና አጽም፤ በቅጫምና በቅማል ያለቀ ገላ ጦራችንን በዝረራ አሸንፎ ክላሽና መትረየስ ተሸክሞ፤ የነተበ እራፊ ጨርቅ ከላዩ አድርጎ ወደየነበርንበት ከተማ ሲገባ ተመልክተናል፡፡ ግንቦት 1983፡፡ በእውነት ረሀብና ጥማት መታረዝና መታፈን መሞት፤ እንዳለ ሳያውቁ ከሆነ ግንባር ድረስ የተጉዋዙት በርግጥም ወይ የነአንዳርጋቸው ስህተት ነው ወይም ልጆቹ ብስለት አልነበራቸውም፡፡

12-    እንደመሰለኝ በስተርጅና ኤርትራ የሚንከራተተው ወዳጄ አንዳርጋቸው ጽጌም ይሁን ፤ ሌሎች ወታደራዊ ባለሙያዎች በቂ ቅድመ ምክር ወይም መግለጫ ወይም ስልጠና አልሰጡዋቸውም መሰለኝ፤ ለአመታት ትግል ቆርጠው የሄዱት ወጣቶች በሄዱ በጥቂት ወራት ውስጥ ተፈተው እንዲህ ያለው ነገር ተከሰተ፡፡ ግማሾቹም ጠፍተው፤ ግማሾቹም በኤርትራ መንግስትና በግንቦት ሰባት ርዳታ ነፍሳቸው ተርፋ ወደሰላም አገር ሊመጡ ቻሉ፡፡ ያ ሁሉ አልፎ በሰላም ወደውጭ ከወጡም በሁዋላ፤ ልጆቹ በንግግራቸው ቁጥብ አልሆኑም፡፡ የሚበሉትን፤ የሚፈሱትን ሁሉ አንድም ሳስቀሩ መዘርገፋቸው አግባብ አይደለም፡፡ የልጆቹን ኤርትራ ድረስ መሄድ ባደንቅም፤ ወደኤርትራ ሲሄዱ፤ ሲሆን ሲሆን ሞትን፤ አለያም አካል መጉደልን መጠበቅና፤ የመጣው ቢመጣ ያንን በረቃቅሶ፤ እዚው ተሙዋግቶ ለመውጣት መቁረጥ ነበረባቸው፡፡

መለፍለፍን ምን አመጣው፤ ስዬ አብርሀን አናይም እንዴ

13-    ወደሰላም ከመጡ በሁዋላ አገግመውና ጊዜ ወስደው፤ ግራ ቀኙን አይተው ምስክርነታቸው በረጅም ግዜ የአገሪቱ ትግል ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት አጢነውና አመዛዝነው መናገር ወይም አለመናገር ሲገባቸው፤ ባንድ ግዜ ሳይገረፉ ይሄንን ሁሉ ቃል መዘክዘክ የሚያሳፍር ነው፡፡ መፍረድ ከባድ ነው፡፡ አትፍረድ ይፈረድብሀል ተብሎ ተጽፎዋልና፡፡ ግን ደግሞ አንዳንዴ አለመፍረድም ስህተት ነው፡፡ ስለዚህም እፈርዳለሁ፡፡ እነዚህ ልጆች ልክ ህዝባዊ ሀይሉን ለመመስረት ወደትግል ሲሄዱ የፈጸሙትን ስህተት አሁንም ከዚያ አምልጠውም ይሁን ሸሽተው ሲመጡ እየደገሙት ነው፡፡ አንድ ግዜ በግንቦት ሰባት ተታለን ወደ ኤርትራ ሄድን ካሉ በሁዋላ፤ ሁለተኛ ደግሞ በግንቦት ሰባት ዲ ወይንም በግንቦት ሀያ መታለል የለባቸውም፡፡ ለግንቦት ሰባት ዲ የሰጡት ቃለምልልስ እንደሚያሳየው ከሆነ ግን፤ ልጆቹ አሁንም አልተማሩም ወየንም አልተረጋጉም፡፡ ስለዚህ መጀመሪ ይረጋጉ፡፡

14-    እንጂ፤ ከነስዬ አብርሀ አንማርም እንዴ፡፡ ስዬ አብርሀ ያን ሁሉ ውርደት ተከናንቦ ከነበረበት የስልጣን መሰላል ተገፍትሮ ወርዶ ራሱ፤ ተስፋዬ ገብረአብ እንዳለው በስድስት መቶ ገጽ በመጽሀፉ እንኩዋን ስለተከሰሰባቸው መኪኖች ሻንሲ ቁጥሮች ነው የጻፈልን፡፡ ዳኝነት በኢትዮጵያ ብሎ በሕወሀት ውስጥ ስለነበረው ንትርክና ሕዝብ ስለማያውቃቸው የሕወሀት ምስጢሮች ሳይሆን፤ ሁላችንም ስለምናውቀው የኢትዮጵያ ፍርድቤቶች ውሎ ነው የጻፈው፡፡ እሱ ሲያስርና ሲያሳስር፤ ሲፎክርና ሲያባርር እንዳልነበር ሁሉ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ እንደሌለ ማሳያ አድርጎ የመረጠው፤ በርሱና በቤተሰቦቹ የደረሰውን ጭቆና ነው፡፡ ዋናው ነጥብ ግን፤ ያ ሁሉ አልፎም አቶ መለስ ከሞቱ በሁዋላ እንኩዋን፤ አቶ ስዬ አብርሀ ጭራሽ አቶ መለስን በማድነቅና ኢትዮጵን ህዝብ በሞታቸው እንዳዘነ አድርጎ በማውራት አንጀታችንን ሲልጥው ነበር፡፡ ሌላ ምንም ትንፍሽ አላላም፡፡ ታጋይ እንዲህ ነው፡፡ አይለፈልፍም፡፡

የኤርትራ ነገር አዲስ ነገር የለውም፤

15-    ከላይ እንዳልኩት እነኚህ ልጆች ላይ የደረሰባቸው ነገር ያሳዝን ሆናል፡፡ ነገር ግን በተወሰነ መልኩም የልጆቹ ዝግጁ አለመሆንና አለመብሰል፤ እንጂ የሚሄዱት ወደጦርነት እንደመሆኑ መጠን ከዚህም የከፋ ነገር ሊደርስባቸው እንደሚችል መገመት ነበረባቸው፡፡ የኤርትራ ጉዳይም ብዙ አዲስ ነገር የለውም፡፡ እንደውም ኤርትራ የራሳችን ሰዎች እየገቡ የሚፈጥሩት ሽኩቻና የርስ በርስ ንትርክ በጥብጦዋት እንጂ እስካሁን ለተቃዋሚዎች ለምታደርገው ድጋፍ መመስገን ያለባት አገር ነች፡፡ ምንም ይሁን ምን ማንም በኤርትራ በኩል የሚሄድ ኢትዮጵያዊ ታጋይ በዚያ በኩል ያለውን አደጋ የሚያጣው አይመስለኝም፡፡ ያሬዶ፤ ከጠቅስካቸው የግፍ ታሪኮችም እንደምትረዳው፤ ችግሩ ያለው ኤርትራ ጋር አይደለም፡፡ የኛ የራሳችን ሰዎች ጋር ነው፡፡ እኛ ጋር ነው፡፡ ለትጥቅ ትግል የሚሆን ወኔም፤ ቁርጠኝነትም የለንም፡፡ ለዚያ ቁርጠኝነት ያላቸው እዚው ይሞታሉ እንጂ ሸሽተውም አምልጠውም አይወጡም፡፡ አሁን ሌሎች አንተ ጽሁፍ ላይ ስላስተዋልኩዋቸው ጥቃቅን ስህተቶች ልናገር፡፡

አንዱን ወገን ብቻ ያደመጠ፤ ስሜታዊነት የተንጸባረቀበት ፍርድ

16-    የያሬዶ ጽሁፍህ ላይ ከተስተዋሉት ብዙ ስህተቶች አንዱ፤ ያንዱን ወገን ብቻ ሰምቶ ወደፍርድ የመግባት ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ የልጆቹን ሰቆቃ ከሰማ በሁዋላ ስለክስተቱ በግንቦት ሰባት አመራር በኩል ለማጣራት ያደረግከው ሙከራ እንዳለ አልጠቀሰልንም፡፡ ከምስረታውም ጀምሮ ስላልጣመውና ይሄ የትጥቅ ትግል የሚባልን ነገር ስለማያምንበት ብቻ፤ አስቀድሞ በጭንቅላቱ ስለደመደመ፤ የልጆቹን ታሪክ እንዳለ አምነኖ ተቀብሎዋል፡፡ እኚህ ልጆች በርግጥም ደረሰብን ያሉት በደል ደርሶባቸው ከሆነ፤ አንደኛ ለወራት እረፍትና ህክምና የሚያስፈልገው የአእምሮ መቃወስ ደርሶባቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የሚናገሩትን ሁሉ እንዳለ ለማመን ይከብዳል፡፡ ሁለተኛ ልጆቹ ደህነነት የሚሰማቸው ቦታ እስኪገቡ ድረስ የሚናገሩትን ሁሉ በነጻነት ለመናገራቸው ምንም ዋስትና የለም፡፡ ተቀብሎ ያስጠጋቸው አካል በግንቦት ሰባት ላይ የራሱን ፖለቲካዊ ነጥብ ለማስቆጠር ሲል በቀጥተኛም ባይሆን በተዘዋዋሪ ጫና እያስለፈለፋቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ በኔ አስተያየት፤ በሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ላይ የአመታት ልምድ ያካበተው አቶ ያሬድ ሀይለማሪም፤ በልጆቹ ልቅሶ አዝኖ በስሜት አግባብ ወዳልሆነና ወደተጣደፈ ክስና ወቀሳ የገባ መሰለኝ፡፡

17-    በዚህ ግሩም ጽሁፉ፤ ያሬድ በርግጥም ስሜታዊ ሆኖዋል፡፡ ስሜታዊነቱን ለማሳየትም ከላይ ከጠቀስኩዋቸው በተጨማሪ፤ የተለያዩ ምሳሌዎችን መንቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፤ እርግጥ ነው የግንቦት 7 ልሳን የሆነው ‘ኢሳት’ እንዲህ ያሉ የሕዝብ ብሶቶችን በካድሬ መነጽር ስለሆነ የሚመነዝረው፤ ኢሳት ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች መንፈሳዊ ብርታት ማጣታቸው፤ የሚሉ አላስፈላጊ የሆኑና ጸሀፊው ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት ያዳከሙበትን፤ ብዙ ሰዎች ይሄ ጸሀፊ ችግሩ ሙያዊና ሰብአዊ ነው ወይስ የግል ጸብ ነው ሊያሰኙ የሚችሉ ሀረጎችን አስገብቶዋል፡፡ በነገራችን ራሱን የቻለ ጽሁፍ ቢወጣውምና ኢሳትን በተለያዩ ተያያዥ ሙያዊ ጉዳዮች ልንተች ብንችልም፤ በዚህ የሚያሳፍር ጉዳይ ላይ ኢሳት ጊዜም ገንዘብም አለማባከኑ ብልህነት ነው፡፡

እንደማጠቃለያ፤ አሁንም ቢሆን የኤርትራውን መንገድ መዝጋት የለብንም

18-    እንደማጠቃለያ፤ አረረም መረረም፤ ስለትጥቅ ትግል ስናስብ፤ ከነአደጋውም ቢሆን፤ ያለችው ብቸኛ አማራጭ ኤርትራ ነች፡፡ ኤርትራ እስካሁንም ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሀይሎች ስለምትሰጠው እርዳታ መመስገን አለባት፡፡ ግንቦት ሰባትን ጨምሮ የኛ ፖለቲካ መሪዎች ዝርክርኮችና እንዝህላሎች ሆነው ቢያባክኑትም፤ ኤርትራ ላለፉት አስር አመታት ላደረገችልን ነገር ሁሉ ልናመሰግናት ይገባል፡፡ የራሳችንን ድክመት ኤርትራ ላይ ማላከክ የለብንም፡፡ እነሱ የራሳቸውን ጦርነት ተዋግተው ለድል በቅተዋል፡፡ ካስታጠቁና ስንቅ ከሰጡ በሁዋላ፤ እንዲተኩሱሉን መጠበቅ የለብንም፡፡ አሁን ከኛ በኩል የሚያስፈልገው፤ ዳጉሳ ተራ የሚገኝና የተስፋየየ ገብረአብ መጫወቻ የሚያደርገን መሪ ሳሆን፤ በተቻለ መጠን ከኤርትራ ጋር ግልጽ በሆኑ ነጥቦች ላይ ግልጽ በሆነ መንገድ የሚደራደርና የሁለቱን አገሮች አንገብጋቢና አከራካሪ ጉዳዮች በስርአት የሚዳስስና፤ የሚያዋጋን መሪ ነው፡፡

19-    የኤርትራ መንገድ የማይመቻቸው ካሉ፤ ቢያንስ ሌላው እንኩዋን ነገ እድሉን እንዳይሞክር መንገድ ባይዘጉና፤ እንደደምስ በለጠ ዝም ቢሉ ይሻላል፡፡ ዝም፡፡ እንደውም ሰዎች ከኤርትራ ተርፈው ሲመጡ ዘለው ሬድዮ ላይ ወጥተው የባጥ የቆጡን መዘክዘክ የለባቸውም፡፡ ይሄንን ቃለምልልስ የሚያቀነባብሩትም ገና ለገና ብርሀኑን ወይም አንዳርጋቸውን የጎዱ መስሎዋቸው ነገ እንኩዋን ሰው እንዳይተማመን በሚያደርግ መልኩ ከኤርትራ ያመለጡ ሰዎችን ማስለፍለፍ የለባቸውም፡፡ እንደያሬድ ኃይለማርም ያሉ በሳል የሰብአዊ መብት ተሙጋቾችም የሰላም ሰዓቱን መርህ ከወታደራዊ መርህ፤ የዴሞክራሲን መርህ ከሽምቅ ውጊያ ዲሲፒሊን ጋር በመደባለቅ በሚያነሱዋቸው የተሳሳቱ ክርክሮች ሰውን ማሳሳት የለባቸውም፡፡

ተከልሚካኤል አበበ፤ ቶሮንቶ፤ ካናዳ፤ የካቲት 2006/2014


Print Friendly