ገነት

Sodere.com
ገነት

በሲራክ ሮበሌገነት

 

በዚያች በቀጫጭን ጣውላዎችና ኮምፔንሳቶዎች በተገጣጠመች ትንሽ ግሮስሪ ውስጥ ከጓደኛዬ ጋር ሆኜ ቪኖ በኮካኮላ በርዤ ስጠጣ ነበር ከቆሎ ሻጭቱ ጋር የተዋወቅሁት።

 

ቆሎ የምትሸጥበትን እስከ ወገቡ ድረስ በገብስ፣በሱፍና በሽንብራ ቅልቅል ቆሎ የተሞላ ነጭ ሳህን ይዛ ገባች።ሰውነቷ በአንዲት አሮጌ የፈረንጅ ቀሚስ ተሸፍኗል።ፀጉሯን በነጠላ ዕላቂ ሸብ አድርጋዋለች።በኪዮስኳ ውስጥ አምስት ሰዎች ብቻ ነበርን፤እኔና ጓደኛዬ፣ሌሎች ሶስት ሰዎች።መጀመሪያ ወደሰዎቹ ጠጋ ብላ ቆሎዋን አሳየች።ያስታወሳት አልነበረም።ሶስቱም አልኮል ያቀላቸውን አይኖቻቸውን እያንከባለሉ የስካር ጨዋታ ይዘው ነበር።ወደ እኛ መጣች።ቆሎ እምብዛም አልወድም።ግን እሷን የረዳሁ መስሎኝ ይሁን ወይስ ቪኖው አዞኝ፣

 

“ እስቲ የአስር የአስር ስፈሪልን! ” አልኳት።

 

በተረከዟ ቁጢጥ አለችና በጨርማታው መስፈሪያዋ እየሰፈረች እንደማቅረቢያ ወደምትጠቀምበት የጫማ ቀለም ቆርቆሮ ከዘረገፈች በኋላ ፊት ለፊታችን ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠችልን።ዘገን አደረግሁኝ።ጓደኛዬም ዘገን ቃም አደረገ።እኛ ዕቃዋን እስከምናጋባላት ድረስ ሌላ ቦታ ለመሸጥ ወጣች።ከእሷ መውጣት ጋር የእኔም ስለ እሷ ማሰብ ተዘነጋ።የቆሎውም መቆረጣጠም ተረስቶ ወደ ጨዋታችንና መጎነጫጨታችን ተመለስን።

 

ተመልሳ መጣች።በቀጥታ ዕቃዋን ልታነሳ ነበር።ዕቃዋን ከአነሳች በኋላ ሂሳቧን ለመቀበል አይኖቿን ማቁለጭለጯ አይቀርም።ነገር ግን ገና ያልተነካ መሆኑን ስትመለከት አፈር ብላ ቆም አለች።ቀና ብዬ አየኋት፤አይኖቿ! ግልብጥ ግልብጥብጥ ሲሉ! በዛ በከሳ ፊቷ ላይ የተሰካው አፍንጫ! አይ አሳዛኝ – በልቤ ።

 

አይኖቿ ግልብጥ ግልብጥብጥ ከአሉ በኋላ  የእኔውን አትኩሮት መሸከም አቅቷቸው ሰበር አሉ።

 

“ ነይ እዚህ ተቀመጪ…ዕቃሽ እስኪጋባልሽ ድረስ… ” አልኳት።

ቀና ብላ አየችኝና መልሳ አይኖቿን ወደ መሬት ሰካች።አልመለሰችልኝም።

“ ነይ ነይ ቁጭ በይ! ” ክንዷን ሳብ አድርጌ ከጎኔ አስቀመጥኳት።ዝም አለች።

 

አይኖቿ አሁንም ቀና ብለው አዩኝ፤ጓደኛዬን አዩት፤ሶስቱን ሰዎች አይዋቸው።ተመልሰው ወደ ሳህኑ፣ቀጥሎ ወደ መሬት ተወረወሩ።ድብርት እንደገባት ተረዳሁ።ሀፍረትና ፍርሃት እንዳይሰማት በትህትናና በማባበል አረጋጋኋት።ይበልጡኑ ደግሞ ከስካር ጋጠወጥነት ስሜት የራቅሁ መሆኔን እንድታውቅልኝ የፊት ገለጻዬን፣ እጆቼንና አንደበቴን ተጠቀምኩ።ገና እኮ ልጅ ናት!ግን ማንያውቃል? አካባቢዋን ትመለከት የለ?

 

“ ለስላሳ ጠጪ…ጩጬ! ”

 የሆነ ነገር ተናገረች። አልገባኝም።

“ ለስላሳ ጠጪ አይዞሸ…ማነህ ስማ…ለስላሳ አምጣ! ”

 

አሳላፊው ሚሪንዳ ከፍቶ ሰጣት።የቆሎ ሳህኗን ወለሉ ላይ አስቀመጠች።እኔም ከጓደኛዬ ጋር ጨዋታዬን ቀጠልኩ።ወደ ቆሎ ሻጭቱ ዞር ያልኩት ሚሪንዳዋን ሩብ ያህል እንደተጎነጨች ነበር።አሁን ድብርቷ ለቀቅ አድርጓታል።ቅድም በፍርሃትና በድንግርግር ጨለም ብለው የነበሩት እኒያ መሳሳይ አይኖቿ አሁን ወደ ተፈጥሯዊ ብሩህነታቸው መመለስ ጀምረዋል።

 

“ አይዞሽ ተጫወቺ! ” አልኳት።

“ እሺ! ”

ለጥቂት ሰኮንዶች ዝም አልኩ።ከዚያ በኋላ ነበር፣

“ እንዴት ነው ቆሎው ደህና ይሸጥልሻል? ” ብዬ የጠየቅኳት።

 

አይኖቿን ወደ ቆሎ ማቅረቢያው ወረወረች።ገና አልተቆረጠመም።አይኖቿ በመከፋት ደብዘዝ ያሉ መሰለኝ።በመዳፌ ሙሉ አፈስኩና ቃም አድርጌ በድጋሚ ጠየቅኳት።

“ አይ… ብቻ ብዙም አይደል! ” ብላ ጣራ ጣራ እያየች አሰብ አደረገች “በሙሉ ከተጣራልኝ ከዚህ ሳህን ሁለት ብር አተርፋለሁ።ግን ብዙ ጊዜ አይጣራልኝም:: ”

“ በምትሸጪበት ጊዜ ምንም የሚያጋጥምሽ ችግር የለም? ”

 

እዚህ ላይ ቀና አለች።አሁን ፍርሃቷ የለም።ትርጉሙ በማይገባ አስተያየት አተኮረችብኝ።አሃ! ከጥቂት ቅፅበቶች በኋላ ገባኝ።እኔስ አሁን የሷ ችግርአልሆንኩባትም? ደህና ሸቃቅላ እንዳትገባ አጠገቤአስቀምጬ እያናዘዝኳት አይደለም? ወሬ! ለእሷ ወሬ ምንይጠቅማታል? ገንዘብ እንጂ! ተሰማኝ።

 

“ ምንም የሚያጋጥምሽ ችግር የለም?… እስቲ ደግሞ የሃያ ስፈሪልን፤ቆሎሽ ግሩም ነው! ” ዘግኖ ከመቆርጠም ጋር።

ከመቅፅበት ተነስታ መስፈሪያዋን ጨበጠች።በፊቷ ላይ ደስታ! ቆሎዋን እየሰፈረች፣

“ አዎ ያጋጥመኛል! ” ስትል መለሰች።

“ እንዴት አይነት ችግር ? ” ጥያቄዎቼ ሁሉ ዘዴ-ቢስ ቀጥተኞች ነበሩ።

“ አንዳንዴ ሰካራሞች ይደፉብኝና ሳላተርፍ እገባለሁ።ግን አልፎ አልፎ ከደፉብኝ በላይ ይከፍሉኛል።አንዳንድ ወንዶች ልጆች ደግሞ እየዘገኑብኝ ይሄዳሉ።ደግሞ ትላልቅ ሰዎች ቆንጠር ቆንጠር ሲያደርጉብኝ ሳይታወቅ ብዙ ይጎድልብኛል። ”

“ ትልልቅ ሰዎች ? እንዴት? ”

“ ከስታዲዮም፣ከፊልም ቤት ሲወጡ እንዲገዙኝ ስጠጋ ብዙ ሰዎቸ ትንሽ ትንሽ ቆንጠር ቆንጠር ያደርጉብኛል።ብዙ ይጎድላል ታዲያ።አንድ ቀን ለታ ደግሞ አንድ ባለ መኪና ትንሽ ገፋ ሲያደርገኝ – በመኪናው- ቆሎዬ እንዳለ ተደፋብኝ።ድፍን አምስት ብር ሰጠኝና ደስ ብሎኝ ወደቤቴ ሄድኩ።ቆሎው እኮ ቢያወጣ ቢያወጣ ከአራት ብር አይበልጥም። አንድ ብር አተረፍኩኛ!…ግን በሚቀጥለው ቀን የወደቅሁበት እግሬን አሞኝ ነበር።”

 

ጥያቄ አጠያየቅ አላውቅበትምና “እንዲያው አንዳንድ ሰዎች ሞቅ ሲላቸው አሳስተው ገንዘብ አይሰጡሽም? ” ብዬ መልሷን ተጠባበቅሁ።

“ ኧረ አይሰጡኝም! ብቻ አንዳንዴ የቡና ቤት አሻሻጮች ‘ አምስት ብር ነው ሂሳቡ ’ ሲሏቸው አስር ብር ይሰጧቸውና መልስ አይቀበሉም።ለኔ ግን ሳንቲምም ቢሆን አይተውልኝ! ብዙ ጊዜ ግን እንዲህ አይነት ሰዎች ቆሎ አይገዙም። ”  

 

አሁን ምላሷ እየተፍታታ፣ አንደበቷ እየረታ ስለሄደ ደስ አለኝ።እሷን ለማስደሰት ቆሎዋን ደህና አድርጌ ከካሁላት።አጠገቤ የተቀመጠውን ጓደኛዬንም አመሰግነዋለሁ።ብዙ ሳይናገር በቆሎ አፈጫጨቱ ላይ ብቻ ብዙ ተባበረኝ።የቆሎው ማቅረቢያ በተጋባ ቁጥር ሌላ ቆሎ ስለሚተካበት የእኔና የቆሎ ሻጭቱ ጭውውት ይበልጥ እየደራ ሄደ።ያ ከደቂቆች በፊት ተደብቆ የነበረው የሚያንፀባርቅ ተፈጥሮዋ፣ ብሩህ ፀባይዋ ተገልጦ ፍልቅልቅነትን አመጣች።

 

“ እንዲያው ብዙ ታመሺያለሽ ? ”

“ እንደገበያዬ ነው፣ ቶሎ ከተሸጠልኝ በሁለት በሶስት እገባለሁ።ቶሎ ካልተሸጠልኝ ግን እስከ አራት ሰዓት…እስከ አምስትም እቆያለሁ። ”

“ ሰዓት እላፊ አትያዢም ? ” አላት ጓደኛዬ ኮስተር ብሎ፣ መቀለዱ ነበር።

“ ሰዓት እላፊ ደግሞ ስድስት ሰዓት አይደለ ? ”

“ እሺ ልጅ ነሽ፤አያስፈራሽም ?  ብርድስ አይመታሽም ? ” አልኳት።

“ እህ መብራት እያለ ለምን እፈራለሁ ? ብርድስ ቢሆን ታዲያ ቆሎዬ ቶሎ ካልተሸጠልኝ እንዴት እገባለሁ ? እማዬ እኮ ትቆጣኛለች።ቆሎዬ አልጣራ ከአለኝ አውቄ ብዙ አመሻለሁ፣ እሷ እንቅልፍ እስኪወስዳት ድረስ። እማዬ ጠላ ወይም አረቄ ከጠጣች በጣም ሃይለኛ ትሆናለች።ሌላ ጊዜ ግን በጣም ደግ ናት። ታሳዝነኛለች።እታለም ውጪ ባደረች ጊዜ እማዬ ጠላ ከጠጣች በጣም እፈራታለሁ።”

 

ልበ ቢስ! መጀመሪያ እናትና አባት እንዳሏት ሳልጠይቃት!

 

“ አየሽ ረስቼው! ” አልኳት ብርዝ ቪኖዬን አንዴ ጎንጨት አድርጌ “ ስምሽ ማነው ? ”

“ ገነት ”

“ ወላጆች አሉሽ ? እታለም የምትያት ማናት ? ”

“እታለምማ ታላቅ እህቴ ናት። አባቴ ከሞተ ቆይቷል።ድሮ ገና እኔ ትንሽ እንደነበርኩ ነው የሞተው። ”

“ ምንድን ነበር የሚሰሩት ? ”

“ ዘበኛ ነበር። ”

“ ታመው ነው የሞቱት ? ”

“ አዎ ታሞ ነው፤በሳንባ ነቀርሳ። ”

“ እንዴት አወቅሽ ? ”

“ እነ እማዬ ሲያወሩ ሰምቼ! ”

 

ሌሎች ሶስት ሰዎች ተከታትለው ገብተው ከወደ አንድ ጥግ ተቀመጡ። ገነት አይኖቿን ወደ እነሱ ወርወር ስታደርግ ያዝኳት። ወሬዬን ማቋረጥ ግን አልፈለግሁም።

 

“ አሁን ታዲያ ማን ይረዳችኋል? እህትሽ ስራ አላት? ”

“ ማንም አይረዳንም! እማዬ ጠላና ኧረቄ ትሸጣለች። እኔ ቆሎ እሸጣለሁ።እታለም ሞጃ ናት፤ግን አትረዳንም! ”

“ የት ነው የምትሰራው? ”

 

እዚህ ላይ ገነት አፈር አለች።እፍረት ሲሰማት አይኖቿ ሰበር ይሉና ቀጥተኛ አፍንጫዋ ነፋ ነፋ ይላል።

 

“ እታለምማ…ሆቴል ቤት በር ላይ ነው የምትቆመው። እ…አንድ ቀን እንኳ ዋቢሸበሌ ሆቴል ጋር ቆማ አየኋትና ‘ እታለም ’ ብዬ ሮጬ ስጠጋት ‘ ሂጅ! ሂጅ ከዚህ ! ’ ብላ አባረረችኝ ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እፈራታለሁ። ኦ! እሷ እኮ ሃይለኛ ነች።እማዬን እንኳ አትፈራም! ”

 

 ዋቢሸበሌ፣ኢትዮጵያ፣ገነት፣ራስ ወዘተ… ሆቴሎች በር ላይ ተገትረው መኪና ለሌላ ጉዳይ እንኳ ሲቆም ጥሬ እንዳዩ ጫጩቶች እየተጋፉ የሚሽቀዳደሙትን ቆነጃጅት ለአንዳፍታ በአይነ-ህሊናዬ አስተዋልኩ።

 

“ ታዲያ ምንም አትረዳችሁም ? ”

 

“ አንዳንድ ጊዜ አንድ አምስት… አስር ብር ለእማዬ ትሰጣታለች።ግን ‘ይህ እኔ እሷን ለማሳደግ ካፈሰስኩት ጉልበት ጋር ሲተያይ እንኳን ርዳታ ለለማኝ የሚሰጥ ምፅዋት አይደለም’ ብላ እማዬ ነግራኛለች።እታለም የምትወደው ቅባት…ሽቶ…ቀለም…ልብስ እና ጫማ…እ..ወርቅ መግዛት ብቻ ነው። ገንዘቡ አልበቃ እያላት ሳይሆን አይቀርም እኛን የማትረዳን።አቤት ልብሶቿ ሲያምሩባት! እኔም ሳድግ እንደሷ ነው የምሆነው።ግን እኮ እማዬ ‘ የእህትሽ ስራ መጥፎ ነው ’ ትለኛለች።መጥፎ ከሆነ ታዲያ እታለም ለምን አትከፋም? ሁሌ ደስ እንዳላት ነው።እሷ የምትናደደው ውጪ በምትወጣበት ጊዜ እኔ ልጨብጣት ስጠጋት፣እማዬ ቸግሯት ተበሳጭታ ስትናገራት፣ልብሶቿን ስናበላሽባት ብቻ ነው።እኔም ትልቅ ስሆን እንደሷ መልበስ እፈልጋለሁ።ግን እማዬን አልሰድብም ነበር።ደግሞ ትንሽዬ እህት ብትኖረኝ እንደእታለም አልሰድባትም ነበር።መንገድ ላይ ባገኛት ደግሞ አላባርራትም።ልብስ እገዛላታለሁ፤አብራኝ እንድትሄድ አደርጋለሁ።በፍፁም እንደእታለም ሀይለኛ አልሆንም ነበር።ከእኛ ቤት  ትንሽ ራቅ ብሎ ያሉት የሞጃ ልጆች እንኳ ትንንሽ እህቶቻቸውን አያባርሯቸውም።ለምን እንደሆነ እንጃ እታለም ከመኪና ስትወርድ ይዟት ለመጣው ሰውዬ ወደ እነዚህ ልጆች በር ታሳያለች።ትልቅዬ የብረት በር ነው።ከዚያ መኪናው እስኪርቅ ድረስ ወደበሩ አቅጣጫ ትሄድና ተመልሳ ወደቤት ትመጣለች።”

 

ኪዮሰኳ አሁን በሰዎች ተመልታለች።የሲጋራ ጢስ፣የስካር ትንፋሽና ቃላት አፍኗታል።የገነትን የቆሎ ሳህን በቆረጣ ተመለከትኩት።ትንሽ መጋመስ ይኖርበታል።

“ በይ ገነት ቆሎ ስፈሪና ለሁሉም ሰዎች በየጠረጴዛቸው አስቀምጪ፣ የሃያ የሃያ። ” አልኳት።

 

አጠገቤ የተቀመጠው የጤና ረዳት ጓደኛዬ ፍዝዝ ብሎ ገነትን ሲመለከታት ያዝኩት።በልቡ እሳተ-ነበልባል የሚንቀለቀልበት ወጣት መሆኑን አውቃለሁ።ነገር ግን የመናገሩ ጉዳይ አይሆንለትም።ንግግር አለመቻል ሳይሆን መናገር አለመውደድ ይመስለኛል።አሁንም የገነት ታሪክ እንደመሰጠው ባውቅም ዝም ብሎ ከማዳመጥ ሌላ ቃል መተንፈስ አልፈለገም።

 

ገነት ፊቷ በደስታ አብርቶ ወደ እኛ እንደመጣች፣ “ ታዲያ እታለምን አትወጃትም ማለት ነው? ” አልኳት። ከጠየቅኳት በኋላ ምላሴን በቆረጠው አልኩ በልቤ።

እሷ ግን “ አልወዳትም! ” ያለችኝ ሳታንገራግር ነበር። “ አልወዳትም! አንድ ጊዜ ታማ ሃኪም ቤት እንደተኛች ደስ ብሎኝ ነበር።ብትሞትም እንኳ አታሳዝነኝም ነበር።ግን እሷ ሀይለኛ አይደለች? ድና ወጣች።”

“ ምን ሆና ነበር ሆሰፒታል የገባችው? ” ጓደኛዬ ነበር።

“ እርጉዝ ነበረች።መድሃኒት ጠጣችና ሲያማት ሀኪም ቤት ገባች።”

“ እሺ ከዚያስ? ”

“ በቃ አስወረዳታ! አሁን እኮ ድናለች።”

“ሌሎች እህትና ወንድሞች የሉሽም ማለት ነው? ”

“ የሉኝም! ” በአንገቷ ጭምር ነገረችኝ።”

“ታዲያ መቼም በጠላና በቆሎ ንግድ ብቻ መኖር ያስቸግራል።እንዲያው በቀበሌ ማህበራችሁ በኩል ጥቂት አትረዱም? ”

“ ድሮ ድሮ ለችግረኞች ተብሎ 25 ኪሎ በቆሎ ወይም ስንዴ ይሰጥ ነበር።እሱም ከቀረ ቆይቷል።አንድ ቀንማ እማዬ ከህብረት ሱቅ ሻጩ ጋር ተጣልታ ደብድቧታል!” አለች።ድምጿ የሀዘንና የቁጭት ዜማ ይዟል።

“ ምን አድርጊ ብሎ ደበደባቸው ደግሞ? ”

“ እንግዲህ ቀበሌ ጤፍ መጣና ለኛ ዞን ሲከፋፈል እማዬም ወረፋ ጠብቃ ጠብቃ ሊደርሳት ሲል አለቀ ተባለ።ጤፉ እኮ ግን አላለቀም ነበር።እነ እማዬ ሳንገዛ አንሄድም! ብለው ተቀመጡ።ቀኑ እየመሸ…እየመሸ ሲሄድ እማዬ ተናደደችና እያለቀሰች ወጥታ ‘ አንተ ሆዳም! አንተ ቋትህን እየሞላህ እኔ ጦም ልደር? በሀገሬ የሚበላ ሳይጠፋ ከልጄ ጋር በረሃብ ልሙት? ’ ብላ ተንደርደራ ስትገባ ሻጩ ተከትሏት ገባ።እኔም ደንግጬ ተከትዬ ስገባ ብዙ ዶንያ ጤፍ አየሁ።እማዬም እየጮኸች ‘ ይኼ ሁሉ ጤፍ ታዲያ ለማነው?’ እያለች ስትናደድ እየደበደበ አስወጣት።እሷም ግን በጥፍሯና በጥርሷ ፊቱን እና እጆቹን አበላሽታዋለች።እኔም ሳልቀር እሱንና እናቴን ይጎትቱ የነበሩትን አበዮት ጠባቂዎች በድንጋይ ብያቸዋለሁ።ከዚያ ሁለት ቀን ታማ ተኝታለች።እኔ ነበርኩ ከቆሎ በማገኘው ገንዘብ ዳቦ እየገዛሁ ያበላኋት።ቆሎ መቁላት እኮ በደንብ እችልበታለሁ።እታለም ያኔ ሶደሬ ሄዳ ስለነበር ሳምንቱን ሙሉ አልመጣችም ነበር።”

 

“ ምን እንደሚታየኝ ታውቃለህ? ” አለኝ ጓደኛዬ።

“ እ…” አልኩት የሚታየውን ወይም የሚያቃዠውን እንዲነግረኝ።

“ ከቀበሌም ሆነ ከጉሊት የሚገዛ ነገር አሮባት የተጎሳቆለችው፣የእናቷ ልጅ ከመብለጭለጭ አብልጣ ስላልወደደቻት የኮሰሰችው ቆንጅዬ ልጅ ይቺው፤አጠገብህ አስቀምጠህ እያናዘዝካት ነው።ከሩቁ የሚታየኝ ግን ደሳሳ ጎጆ ነው።በዚያ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ደግሞ ጉስቁልና ከነጭራሹ ደብዛውን ባያጠፋውም ያወየበው መልክ፣ቀጭን ሰውነት፣አጭር ቁመት።በመቀነት ተጠፍሮ የታሰረ አንጀት።አጎበር ያወጡ እጆች።ውርጭ የጠበሳቸው ባቶች።ነጠላ ጫማ የሰነጣጠቃቸው እግሮች-እናቷ! ”

 

ገነት በመገረም ስትመለከተው ቆየችና አንገቷን አቀረቀረች።

“ እውነት አይደለም ገነት? ” አላት።

እፍር ብላ እየፈገገች “ እማዬ…አዎ ቀጭን ናት! ” አለችው።

“ እናትሸ ሲደበደቡ ህዝቡ ምን አለ ታዲያ? ” እኔ።

“ ምንም! ”

“ ለምን ግን? ” ለራሴ ነበር።

“ እኔ እንጃ! ” ገነት ተቀበለችኝ “ ግን እማዬ እንደምትለው ‘ ዛሬ ቀበሌን ተናግረን ነገ የት ልንገባ ነው?’ እያሉ ነው። እማዬ ግን እኮ አትፈራም።ሃይለኛና ደግ ናት። ብዙዎቹ ጎረቤቶቻችን እንደኛው ድሆች ናቸው።ግን ይፈራሉ።እሷ ምንም አይመስላትም። ‘ ምን እንዳይቀርብኝ ነው?ቀድሞ ያው ነበርኩ፡ አሁንም ያው ነኝ!ግፋ ቢል አንድ ሞት ነው!’ እያለች ስትናገር በዙ ጊዜ ሰምቻታለሁ።ጎረቤቶቻችን በሰውነት ከእማዬ ትላልቆች ሆነው እንኳ ዝምብለው እምምምም…ይላሉ እንጂ ቀበሌዎችን አይናገሩም። በጣም ፈሪዎች ናቸው! ”

 

ገነት ይህን ስትናገር በፍርሃት፣በድፍረት፣በሀዘን፣በንዴትና በማሾፍ ስሜት ነበር።እንደእየቃላቱ ዜማዋንና ስሜቷን የመለዋወጥ ልምድ ነበራት።ጣፋጭ ቆሎዋ ወደ መገባደዱ አለ።የኪዮሰኳ ጠጪዎች ሁሉ ስለተባበሩን ቆሎው ሸፍኖት የነበረው የሳህኑ ውስጠኛ ክፍል እየተጋለጠ…እየተጋለጠ…ሲሄድ፣የገነት አይኖች እያበሩ…እያበሩ…ሲያምሩ ጨዋታችን እየሞቀ…እየጋለ…ሄደ።ተደሰትኩ።

 

“ አሁንስ ምን ታየህ? ” ስል ጠየቅኩት ጓደኛዬን በጨዋታችን በመሳተፉ ደስ ብሎኝ።

“ ከማህፀኗ ወጥቼ ግን ስለእናት ሀገሬ አሁንም ገና ብዙ ያላወቅኩ ነኝ።ከእኔ ደደብነት የተነሳም ይሁን አላውቅም አሁንም ሀገሬ የደበቀችኝ ምስጢር ያለ ሆኖ ይሰማኛል።ይህ በማመንና ባለማመን፣ በመጥፎና በቅን ተመልካችነት መሀል እንድወዛወዝ አድርጎኛል።የገነትን እናት ያጠራጠራቸው፣ያበሳጫቸውና የተወለዱባትን መሬት እንዲረግሙ የገፋፏቸው እነማን ናቸው? ይኸውልህ የገነት እናት ከቀበሌያቸው ኗሪዎች ጋር ተሰብስበው አየኋቸው።በርካታ ሳጥኖች ፎቶግራፎች ተለጥፈውባቸው ተደርድረዋል።እሳቸው ዕላቂ ነጠላ ተከናንበው ደስታ-ቢስ ፊታቸውን ከፀሀይ ከልለዋል።በእጃቸው የያዟቸውን ካርዶች ያለ-ስሜት ይመለከቷቸዋል።ከደቂቃዎች በኋላ በእየሳጥኑ ከተው ተመለሱ።አይበቃህም? ”

“ እንዲያው ከቀበሌ ተመራጮቻችሁ ውስጥ…እንዲያው ጥሩ ሰዎች የሉም? ” ከማለቴ ከአፌ ነጠቅ አደረገችና፣

“ አሉ ” አለች ሳቂታ ተፈጥሮዋን ይበልጥ እያሳቀች “ ሊቀመንበሩ በጣም ጥሩ ሰው ናቸው።ከእማዬ ጋር እንኳ ቀበሌ ስንሄድ በደንብ ነው የሚያነጋግሩን።ምክትል ሊቀመንበሩ ግን በጣም ክፉ ሰው ናቸው።አቤት እማዬንማ ሲጠሏት! ” የገነት ፊት ተለዋወጠ።ስለ ቀበሌያቸው ሊቀ መንበር ስታወራ የፈካው ገጿ አሁን ስለ ምክትሉ ስታወራ ጠቋቆረ “ ስለምትናገራቸው ሳይሆን አይቀርም።ደግሞ በጣም ይኮራሉ።እነ እትዬ ነዲ ሲሉ የሰማሁት ለቀበሌ ከተመረጡ በኋላ ነው መኩራት የጀመሩት።እማዬ እንደውም ቀበሌን የምትጠላው በእኚህ ሰውዬና በህብረት ሱቅ ሻጩ ምክንያት ነው። ‘ ምን! ቀበሌ ማለት ጓድ መርሻ እና ጓድ ተክሌ ማለት ነው! ’ ትላለች ሁሌ!”

“ መርሻ እና ተክሌ እነማን ናቸው? ” ስል አቋረጥኳት።

“ ጓድ መርሻ ምክትል ሊቀ መንበሩ ናቸው፤ ጓድ ተክሌ ደግሞ የህብረት ሱቅ ሻጩ ነው።አንድ ሰውዬ ደግሞ አሉ፤ እሳቸውም ተመራጭ ናቸው።እማዬን በደንብ ካነጋገሯት በኋላ ሳታያቸው ከኋላዋ ሲያሾፉባት መዓት ጊዜ አይቻቸዋለሁ።እማዬ ግን ደስ ብሏት ነበር ወደ ቤት ስንሄድ።እንዳሾፉባት እኮ አልነገርኳትም።ከነገርኳትማ ሃይለኝነቷ ይነሳባትና ትደበደባለች።”

 

ገነት ይህን ከጨረሰች በኋላ አንገቷን ሰበር አደረገች።ሰዓቱ በመገስገስ ላይ ነው።ሰዓት አልነበረኝምና ጊዜውን በትክክል አላወቅኩትም።ጓደኛዬም አላሰረም።ሆኖም  ወደ አንድ ሰዓት ይጠጋል ብዬ ገመትኩ።ይመሽባታል ብዬ አልተጨነቅኩም።ወሬዋ በጣም ጥሞኛል።በዚያ ላይ ደግሞ ማምሸትን የለመደችው ጨቅላ ዛሬም ብታመሽ ምንም እንደማትሆን ይሰማኛል።እሷ በዚህ መሪር-ጣፋጭ ወሬዋ ውለታ እንደጣለችብኝ ሁሉ እኔም አጠገቤ አስቀምጬ ከብርድ አድኛታለሁ።ለስላሳ ከመጋበዜም በላይ ቆሎዋን አጣርቼላታለሁ።ታዲያ ይህ ውለታ መመለስ አይባልም እንዴ? 

“ ለመሆኑ ትማሪያለሽ? ”

“ አዎ ሁለተኛ ክፍል ነኝ። ”

“ ስንት አመትሽ ነው? ”

“ አስር።”

“ ትምህርትሽን ተከታተይ! አየሽ ከተማርሽ ነው እናትሽንና ራስሽን ልትረጂ የምትችይው። ”

“ ግን እኮ እታለምም ከአምስተኛ ክፍል ነው ትምህርቷን ያቋረጠችው።ግን ይኸው ሞጃ ናት።”

“ እንደሱ አይደለም ገነት!የእታለም አይነት ስራ ወደፊት ቦታ አይኖረውም።ከፍ እያልሽ ስትሄጂ ትለይዋለሽ።እነሱ የሚሰሩት ስራ ህግ ያልፈቀደው፣ ጤናን እና ሰውነትን የሚጎዳ መጥፎ ስራ ነው።ገባሽ? የእነሱ ስራ ኢትዮጵያን…ሀገርሽን ማለት ነው…እ? ”

“ አውቃለሁ። ”

“ ሀገርሽን ኢትዮጵያን የሚያዋርድ ስራ ነው።አንቺን፣እናትሽን፣እኔን፣እሱን የሚያሰድብ ስራ ነው።ስለዚህ ይህን ሀሳብ ሁለተኛ አታስቢ!አንቺ ማለም ያለብሽ ከፍ አድርገሽ ነው።ተምረሽ፣አውቀሽ እናትሽን፣አንቺን ከሁሉም በላይ ደገሞ ኢትዮጵያን የምታገለግይ መሆን አለብሽ! ”

 

ገነት ትኩር ብላ በህፃን ተመስጦ ብታዳምጠውም በነገሩ ትመንበት አትመንበት አላወቅንም።ጓደኛዬ ንግግሩን ቀጠለ።

“ አንድ ጊዜ እኔው መስሪያ ቤት ለህክምና ተኝቶ የነበረ ደቡብ አፍሪካዊ ስደተኛ ዘይ አር ዘ ደርት ኦፍ አዲስ ያለኝን አልረሳም።እታለምና ጓደኞቿ የኢትዮጵያ ነቀርሳ ናቸው።በእርግጥ ድህነት ምክንያት ሊሆን ይችላል።ቀን ቀን ስራ እየሰሩ ማታ ማታ በሽፍንፍን የሚሸቅሉትስ? ከመልካም ቤተሰባቸው ጉያ ወጥተው የመልአክት አምሳያ ነው ብለው በሚገምቱት መልካቸው፣ በማራኪ ልብሶቻቸውና በቄንጠኛ መጫሚያዎቻቸው ሃይል ብቻ ለመኖር የሚፈልጉትስ? የልጆቹን እናት ከቤት ጥሎ እነ እታለምን የሚያሳድደው አለሌ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ርካሽ የወሲብ ዕቃ ይሸጣል የተባለ ይመስል እነ እታለምን ለማሳደድ ባህር አቋርጦ የመጣውም የውጪ ዜጋ እኩል ተጠያቂዎች ናቸው። ” የጤና ረዳት ጓደኛዬ በግለት ንግግሩን ቀጠለ “ለእነ እታለም መፈልፈል ተጠያቂው የቀድሞው ስርአት ቢሆንም ሁሌ ያለፈውን በማውገዝ ጭንብል ድክመታችንን መሸፈን የለብንም።ያሁኑ መሻሉን የምናሳየው በቀድሞው ላይ ሲደረጉ ያወገዝናቸው ድርጊቶች እንዳይደገሙ ስንከላከል ነው።እነ እታለም ድሮ ተፈልፍለዋል፤ አሁንም እየተፈለፈሉ ናቸው።ድህነትና ረሀብ ድሮም ነበሩ፤አሁንም አልጠፉም።እኔ አንድ ተራ የኢትዮጵያ ዜጋ ነኝና በምን አይነት መንገድ ርምጃ መወሰድ እንዳለበት አላውቅ ይሆናል።ነገር ግን በልቤ ጥልቀት ውስጥ አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት ይሰማኛል። ”

 

ይህ ሁሉ ገነትን ገብቷት ይሆን? እንዳየኋት ከእድሜዋ በላይ በስላለች፤ እና ለመረዳት ብዙ የምትቸገር አይመስለኝም።ይግባትም አይግባትም ጓደኛዬ ተናገረው።እሱ ይህን ሲናገር ድንገት የወጣት ማህበራት ትዝ አሉኝ።

“ እህትሽ የወጣት ማህበር አባል ናት? ”

“ እኔ እንጃ! ”

“ የወጣት ማህበራት ሊቆጣጠሯቸው አይችሉም? ” ስል ጓደኛዬን ጠየቅኩት።

 

ያቀረቀረ አንገቱን ቀና አደረገና “ ሰማህ? የወጣት ማህበራት አባላት ናቸው እነ እታለም።በርግጥ ሁሉም የወጣት ማህበራት አባላት ናቸው ማለቴ አይደለም።ደግሞም የወጣት ማህበራት አባላት ሁሉ ይህን ያደርጋሉ ለማለት ፈጽሞ አልሞክርም።ወጣት ማህበራት አባላቱን ሊቆጣጠሩ ቢችሉም ቁጥጥሩ ገደብ አለው።ከዲሞክራሲ መብት መሰረታዊ ጥያቄ ጋር የሚቃረን መሆን የለበትም።ቁጥጥሩ ከግል ቂም በቀል፣ ከጀብደኝነትና ከድንቁርና ፍፁም የተላቀቀ መሆን ይገባዋል።ከሁሉ ይበልጥ ግን ልንቆጣጠረው የሚገባን ድህነታችንን ነው።” ጓደኛዬ ብርዝ ወይነ-ጠጁን አንዴ ጅው አደረገና የምሬት ንግግሩን ቀጠለ “ ወጣቱን ለመቆጣጠር ግን  የመረጣቸው ተወካዮቹ  መጀመሪያ ራሳቸውን መቆጣጠር መቻል አለባቸው።አንዳንዶቹ ከምሽቱ ስድስት ሰዓት በኋላ የመጠጥ ቤት አዘግተው በመጠጥ ሲንቦራቹ በሌሊት የጥበቃ ተረኝነቴ ጊዜ ይዣቸዋለሁ።”

 

የጤና ረዳቱ ንግግሩን ጨረሰ።እኔም የመጨረሻይቱን ብርዝ ወይነ-ጠጅ ጨለጥኩ።ኪዮሰኳ ሞቅ ደመቅ ማለቷን ቀጥላለች።ጓደኛዬ አዲስ የቀዳውን ብርዙን እስኪያገባድድ ድረስ ጠረጴዛው ላይ የተጋደመ መጽሀፉን አንስቼ ገልበጥ ገልበጥ አደረግኩት።የፑሽኪን ምርጥ ስራዎች ነበር።ድንገት አይኖቼ ማሪያ ቮሎኮንስካያ ላይ ኧረፉ።ዕቃዎቿን በመሰባሰብ ላይ የነበረችው ገነትም አይኖች ወይዘሮዋ ላይ ተተክለው ቀሩ።ማሪያ እንደድመት ፊት ክብ በሆነ ገጿ ላይ ጎላ ጎላ ያሉት አይኖቿ፣ቀጥ ብሎ ወርዶ ጫፉ ላይ ለአመል ሰፋ ያለው አፍንጫዋ፣ የተገጠሙት ስስ ከንፈሮቿ ደስ ይላሉ።በጠቅላላው ጌጧን ትተን ሀዘን የሚነበብባት ወይዘሮ ቆንጆ ነች።ቆሎ ሻጭ ገነት ግን ከእሷ እንደምትበልጥ ከልብ እመሰክራለሁ።

 

ለባለ ኪዮሰኩ የመጠጡን፣ ለገነት የቆሎዋን ሂሳብ ከፍዬ ወጣን።የአዲስ አበባ ስታዲዩም ከፊት ለፊታችን ይታያል።ባሻገር ሌሎች ህንጻዎች ላይ እንደሰው ልጅ ዕድል ቦግ እልም የሚሉት መብራታዊ ማስታወቂያዎች ከተማዋን አሳምረዋታል።የተደረደሩ መኪኖች፣ላይና ታች የሚራወጡ ተሽከርካሪዎች፣ቁጥራቸው የቀነሰ ታክሲ ተሳፋሪዎች፣ሰክረው የሚወላገዱ እና ሰክረው እየዘፈኑ ለመንገዱ ጫጫታ ድርሻቸውን የሚያበረክቱ ጠጪዎች ጎዳናውን ባይሞሉትም አስጊጠውታል።

 

ለመጨረሻ ጊዜ ከገነት ጋር ስንለያይ አይኖቿ አብረቅርቀው፣ፊቷ ፈክቶ ነበር።በእንግልት  የተሸፈነውንና ድንገተኛ ደስታ ሲያጋጥመው ዓይነ-ርግቡን አግልሎ ብቅ የሚለውን ሳቂታ ተፈጥሮዋን አደነቅኩት።ወዲያው ከፊት ለፊታችን ሳህኗን ተሸክማ ንፋሱ ቀሚሷን እያነሳባት ብር ስትል ጥቂት መንገድ ድረስ በአይኔ እየተከተልኩ አንድ ቀን እንደገና ባያት ተመኘሁ።

 

ስታዲዮም መኪና ማለማመጃው ጋር ጓደኛዬን ከመሰናበቴ በፊት ቀና ብዬ የተገተረውን የፊያት መብራት ብመለከት ሁለት ተኩል ይላል።

“ ነገ ተረኛ ስለሆንኩ ቶሎ ልግባ! ” አለኝ መኪና ማለማመጃው ጋር እንደደረስን።

 

ተስማማሁ።

 

ቶሎ ወደቤት መግባት አልፈለግኩም።የዛሬው ድንገተኛ አጋጣሚ የፈጠረብኝን ስሜት እያውጠነጠንኩ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች  ላይ ጥቂት ለመዘዋወር ወሰንኩ።በራንዴቩ ሰገነት፣በመናፈሻ፣በቤተ-መንግስት ዞሬ ኢትዮጵያ ሆቴል ደረስኩ።ከዘንባባ ዛፎች ስር እና ዙሪያ የተገተሩትን ኢትዮጵያውያት እንደተማላ አየት አደረግኳቸው።ከዚያ በቀጥታ በብሄራዊ ትያትር ጀርባ አድርጌ ወደ ሰፈሬ አመራሁ።አሁን ሀሳቤን ሁሉ አስቤ፣ስሜቴን ሁሉ ሰምቼ ወደማገባደዱ ላይ ነበርኩ፣በርግጥ የሚገባደድ ከሆነ።አለያም በመጠኑ ቀለል ብሎኝ ነበር።ዋቢሸበሌ ሆቴል ጋር ስደርስ እንደልማዴ አሁንም የቆሙትን ቆነጃጅት ገልመጥ ገልመጥ ብዬ ማየት ነበረብኝ።አየኋቸው!

***

በማግስቱ ረፋዱ ላይ መስሪያ ቤት ስልክ ተደወለልኝ።ጓደኛዬ ነበር።ድምፁ ውስጥ የሰማሁት ቅጠ-ቢስነት አላስደሰተኝም።

“ ትላንትና ሳይቸግርህ ከቪኖ ጋር የሰው ልጅ ህይወት ምሬት ጋብዘኸኝ እንቅልፍ አጥቼ አደርኩ! ” አለኝ

“ ከሰላምታ በፊት እሮሮ መቅደም አለበት? ” ብዬ ሳቅኩ።

ጓደኛዬ አልሳቀም።

“ ምናባክ ሆነሃል? ” አልኩት

“ በመስኮት ኮከብ ስቆጥር ነው ያደርኩት፤ሰማያዊ፣ቀይ፣አረንጓዴ ኮከቦች።የቀዘቀዘ ራቴን እንኳን አልበላሁም።ኮከቦቹ ገነትን፣እናቷንና እህቷን ሲያንጸባርቁልኝ አመሹ። ”

“ ይህ ታዲያ እንቅልፍ የሚነሳ አልመሰለኝም! ”

“ በጭራሽ አይነሳም! ሌሊቱን ግን በቅዠት ሞላብኝ።ህይወት ቅዠት መሆኗን ቀደም ሲል ተረድቻለሁ።ሌላው ቢቀር እንቅልፌ ነፃ ቢሆን እመርጥ ነበር። ”

ጓደኛዬ  መጥፎ ተመልካች  እስኪባል ድረስ ጥምም ያሉ ሀሳቦችን እንደሚሰነዝር ስለማውቅ ንግግሩ አልደነቀኝም። ያስፈራራኝ ድምፁ ብቻ! አንዳች ተስፋ መቁረጥ፣አንዳች ምሬት የተሞላ ነበር።

“ ያንተ ቪኖ መዘዝ…” ከማለቱ፡ “ የዛሬውን ይቅርታ! ለሁለተኛው ከሻይና ከቡና በላይ አልጋብዝህም! ” አልኩት።

“ የጠላሁት ቪኖህን አይደለም።በቪኖ ሰበብ የሰውን ልጅ ኮሳሳ ህይወት ታሪክ ግብዣህን እንጂ! ”

“ መቼም የገነት ታሪክ ያን ያህል ያሳሰበህ አይመስለኝም።”

“ ማሳሰብስ አላሳሰበኝም! አቃዠኝ እንጂ! ከዚያም አልፎ መንፈሴን በሳሰከው እንጂ!  አሁንም ድረስ እየሸነቆረኝ ነው፣ልቤን!”

 

ድምፁ ምንድነው?!

 

“ አየህ ማታ አንተ ባታስተዋውቀኝ ኖሮ አሁን እንደልማዴ በከንፈር መጠጣ ብቻ አልፈው ነበር።ግን አልቻልኩም። ያን አንደበት ከሰማሁ…ያን እንቡጥ ህጻንነት ካየሁ በኋላ በከንፈር መጠጣ ብቻ ማለፍ እንዴት ልቻል?እዚህ አጠገቤ እናቷ በድኗን ታቅፈው ሲያለቅሱ፣እህቷ እንደነገሩ ለብሳ አስሬ ‘ እንፍ! ’ ስትል እያየሁ እንዴት በከንፈር መጠጣ ብቻ…” ድምፁ ተንቀጠቀጠ።ማልቀሱ ነው እንዴ?

“ ምን እያወራህ ነው?! ” ድንጋጤ እና መደናገር ወረረኝ።ምናልባት ጓደኛዬ ማበዱ ይሆን? ወይስ? ስልኩን የያዘው እጄ ሲንቀጠቀጥ፣ልቤ ድው ድው ሲል ይሰማኛል።

 

“ አጋጣሚው የሚገርምም የሚዘገንንም ነው።ገነት ትላንትና ከእኛ እንደተለየች መኪና ገጭቷት እዚህ ሆሰፒታል ገብታ ኖሯል።እና አሁን ከግማሸ ሰዓት በፊት አርፋለች! ”

 

በድን ሆንኩ።

 

“ የገጫት በስካር ሲያሽከረክር የነበረ የውጪ ሰው ነው።የሚደንቅህና የህይወትን ቅዠትነት የሚያረጋግጥልህ ነገር ደግሞ እታለምም በገጪው መኪና ውስጥ መኖሯ ነው።እህት እህትን ሲገድል አይገርምህም? ቅዠት አይደለም? እኔና አንተስ ለገነት ሞት ሳናውቅ ድርሻችንን አላበረከትንም ትላለህ? ምናልባት ቀደም ወይም ዘግየት ብላ ሄዳ ቢሆን ኖሮ ይህን አደጋ ታመልጥ ይሆን ነበር፤ ማን ያውቃል? ”

 

እሪሪሪሪሪ! ብለህ ጩህ ጩህ አለኝ።

የሞት ሞቴን   “ እውነትም ህይወት ቅዠት ናት! ” ያልኩት መሰለኝ።

“ በጣም እንጂ! የገነትም እናት ሲቃዡ ገነትን ‘ገነት’ አሏት እንጂ እሷስ ሲኦል ነበረች።የምታቃጥል ሳትሆን ራሷ የምትቃጠል ሲኦል! ”

“ አሁን መጣሁ!” ብቻ ነበር ያልኩት…

 

መጋቢት 1974

 

 

 


Print Friendly