“ፀጥታ አትንሱኝ”

“ፀጥታ አትንሱኝ”
አማትና ምራት ተቃቅረው ነበርና ባልቴትዋ ልጃቸውን እንዲህ ይሉታል፡፡
ባልቴት፡- ይህችን ፈትተህ ሌላ ባለሙያ ሚስት ካላገባህ አብሬህ አልኖርም፡፡ ቤቱን ለቅቄልህ እሄዳለሁ፡፡ እሷ እንደሁ ተጎልታ ነው የምትውለው፡፡ ቤት ስጠርግ እንኳ ዝም ብላ ነው የምትመለከተኝ፡፡

ልጅ፡- አየሽ እማዬ፤ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ሳይሆን ቀስ ብለን ብናሳያት እኮ ትለምዳለች፡፡ ለምሳሌ አንቺ ቤቱን ስትጠርጊ “እኔ ልጥረግ እማዬ ስልሽ” እሷም “የለም እኔ ልጥረግ” ብላ መጠረጊያውን ሳትቀበልሽ አትቀርም በማለት ያግባባቸዋል፡፡

ታዲያ እናትና ልጅ በዚያ ዘዴ ተስማምተው ልጅቷን ለማሰልጠን አንድ ዕለት እናቱ ቤት መጥረግ ይጀምራሉ፡፡ ልጃቸውም ጠጋ ብሎ “እማዬ ለእኔ ልቀቂልኝ እኔ ልጥረግ” ይላቸዋል፡፡ እናትም “ግድ የለም ምን ይጎዳኛል.. እኔ እጠርጋለሁ” በማለት እናትና ልጅ ሲጨቃጨቁ ሚስት ታይና “ኧረ እባካችሁ ፀጥታ አትንሱኝ” ለምን ተራ ተጋብታችሁ አንዳችሁ ዛሬ አንዳችሁ ደግሞ ነገ አትጠርጉም?” አለቻቸው ይባላል፡፡ “ይብላኝ ለወለደሽ ያገባሽስ ይፈታሻል” የሚባለው የዚህች ዓይነቱ ሲያጋጥም እኮ ነው፡፡
(አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ የካቲት 17 ቀን 1976)


Print Friendly