Essias Belachew ..ጠርጥር

..ጠርጥርጠለፈ ቢሉኝ – ሚስት ነው ብዬ
ጠለፈ ቢሉኝ – መስኖ ነው ብዬ
ጠለፈ ቢሉኝ – ዳንቴል ነው ብዬ
ለካስ ፕሌን ኖሯል አረገኝ አንተዬ::

እንዲህ የታደለ የአንተን የአመት ደምወዝ በወር የሚቆጥር
እንዲህ የተማረ ሒሳቡን ፊዚክሱን ደህና አርጎ ሚያበጥር
እንዲህ ሺ እግር ያለው አውሮፓ አሜሪካ ባሻው የሚነጥር
ምን ቁርጥ አድርጎት! እዚህ ጣጣ ገባ? ጎበዝ አንዳች ጠርጥር::

እንደነ ሬድዋን እንደነ በረከት
ለውሸትህ ልጏም ሳታበጅ ለከት
‘እብድ ነው’ በልና አስወራ በእህቱ
‘ያመው ነበር’ ብለህ አስነግር በአጎቱ
መቼም እናውቃለን
ሰው ብልጥ ሆኖ ሲገኝ ይህ ነው ዳረጎቱ::

ወይ እንደ ብዙዎቹ የፌስቡክ ወስላቶች
እንደ ብዙዎቹ የቱዊተር ሰላቶች
የተቃዋሚ ፓርቲ ተቀጥላ ላቶች
አርገህ ፓለቲካ
‘ቢሮክራሲው መሮት
ወያኔ አስቸግሮት’
ነው በልና እ…..ሪ! በል ጩኸትክን አስነካ
ጠላትህን ተበቀል ጥማትህ አርካ
አገር እንደነሳህ አገር ባትነሳው
ወገን እንዳሳጣህ ወገን ባታሳጣው
ጉዱን አፈረጥረህ!
ድክመቱን አጋልጠህ!
በአለም ፊት አዋርደው በአደባባይ ቅጣው::

አይ ካልክ ደግሞ በባዶ ሜዳ ላይ ካስጠላህ ማንባረቅ
አሊያም ከፈራህ አሳዶ እንዳይመታህ ከሁለቱ የአንዱ መብረቅ
ምድረ ተቃዋሚ ምድረ ገዢ ነኝ ባይ
ምድረ አለቅላቂ ምድረ ቀጣፊ አባይ
ወደዚህ ሲሯሯጥ ወደዚያ ሲራኮት
እንደዚህ ሲፋተግ እንደዚያ ሲሻኮት
አንተ ዝም ብለህ እይ በላፕቶፕህ መስኮት
በጊዜ እስኪገለጥ የሀቁ መለኮት::

ብቻ ግን አትርሳ
እንዲህ የታደለ የአንተን የአመት ደምወዝ በወር የሚቆጥር
እንዲህ የተማረ ሒሳቡን ፊዚክሱን ደህና አርጎ ሚያበጥር
እንዲህ ሺ እግር ያለው አውሮፓ አሜሪካ ባሻው የሚነጥር
ይጠልፈው ሳያጣ አውሮፕላን ሲጠልፍ ጎበዝ አንዳች ጠርጥር::


Print Friendly